ምስሎችን በመጠቀም የሚደርስ ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭት፦

6
ባሕር ዳር: መጋቢት15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች መነሻቸው ለበጎ ዓላማ ነው። ነገር ግን በሰው ልጅ የትግበራ ልዩነት ለጥፋት ዓላማም ሲውሉ ማየት የተለመደ ነው።
በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚጋሩ የጽሑፍ፣ የፎቶ እና የቪዲዮ ይዘቶች ዘመን የወለዳቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ሳቢ እና ተወዳጅ እንዲኾኑ ማድረግ አሁን ላይ ቀላል ነው።
ፎቶ ግራፎች እና ቪዲዮዎች ላይ የተለያዩ ውበት ፈጣሪ ልውጠቶችን በመጠቀም የጥራት ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ የፎቶ እና ቪዲዮ ኤዲቲንግ መተግበሪያዎች አገልግሎት ላይ ይውላሉ።
በሌላ መልኩ ደግሞ ምስሎች ላይ ሌላ ተጨማሪ ይዘት በመጨመር የሀሰት መረጃ ለማስተላለፍ፣ ለማጭበርበር፣ የሰውን ዝና እና ክብር ለማጉደፍ ቴክኖሎጂ ያመጣቸው መገልገያዎች አገልግሎት ላይ ሲውሉ መመልከት እንግዳ አይደለም።
በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በቀላሉ ሰዎችን ለማሳሳት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ይዘቶች ውስጥ ፎቶግራፍ የመጀመሪያው ነው። ትክክለኛው ፎቶ ላይ ጊዜን፣ ቦታን እና ኹኔታን የሚያመላከቱ የምስል መግለጫዎችን በመቀየር የማሳሳት እና የማጭበርበር ተግባራት ይፈጸማሉ።
ስለዚህ የፎቶግራፎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ምስሉ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ መዋል አለመዋሉን፣ ምስሉ ላይ የተለየ ነገር መኖር አለመኖሩን፣ ምልክት የሚኾን የምናውቀው ነገር መኖሩን እና አካባቢው ምን እንደሚመስል በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል።
የቴክኖሎጂ መዘመን በምስሎች የሚፈጸም ማጭበርበርን ውስብስብ እያደረገው በመምጣቱ ምስሎችን በዐይናችን ብቻ በመመልከት በጥልቀት መርምረን ለመረዳት እና ለመለየት አዳጋች ኾኗል።
አጋዥ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የተጭበረበሩ ምስሎችን በጥልቀት እና በጥራት የምንለይባቸው መንገዶች መኖራቸው ደግሞ መልካም ነገር ነው።
ብዙ ዓይነት ምስል ማጣሪያ አሉ። የተለመዱ እና ለአጠቃቀም ቀላል ከኾኑት ውስጥ ጉግል ሪቨርስ ኢሚጅ ሰርች፣ ቲን አይ እና ፎቶ ፎሬንሲክ ተጠቃሽ ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleባለፉት ወራት በአማራ ክልል ከ469 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።
Next articleየአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር አዲስ ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ሦሥተኛውን ቅርንጫፍ አስጀመረ።