“ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎችን ስመለከት እንባ ይተናነቀኛል”

35
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት በባሕር ዳር ጎዳናዎች ላይ የደንብ ልብስ( ዩኒፎርም) የለበሱ ተማሪዎች የደብተር መያዣቸውን አንግተው ወደ ትምህርት ቤት ይተምማሉ።
በእነርሱ መካከል ደግሞ ዕድሜው ከእነርሱ የማይበልጥ፣ ነገር ግን የትምህርት ቦርሳ ሳይኾን የፀረ-ተባይ መድኃኒት ዘንቢል እና የድምጽ ማጉያ (ጅፓስ) የተሸከመ አንድ ታዳጊ ይታያል። ስሙ ተመስገን አይሸሽም ይባላል።
የ16 ዓመቱ ታዳጊ የተወለደው በሰሜን ጎጃም ዞን ነው። እንደዛሬው ሳይኾን በትምህርቱ ሁልጊዜም አንደኛ በመውጣት ቤተሰቦቹን ያስደስት ነበር። አሁን ግን በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ከራቀ ሦሥት ዓመታትን አስቆጥሯል።
ዛሬ እጆቹ ብዕር ሳይኾን የአይጥ እና የበረሮ ማጥፊያ መድኃኒት ይዘዋል፤ ጆሮዎቹ የመምህራንን ትምህርት ሳይኾን የራሱን የድምጽ ማጉያ ይሰማሉ።
“የደብተር መያዣ ተሸክመው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎችን ስመለከት ውስጤ ይረበሻል፤ እንባ ይተናነቀኛል” ይላል ታዳጊው
ታዳጊው እንደሚለው ቤተሰቦቻቸው የተሻለ አቅም ያላቸው ጓደኞቹ ከተማ ገብተው ትምህርታቸውን በመቀጠላቸው አሁን 11ኛ ክፍል ደርሰዋል።
የእርሱ ቤተሰቦች ግን የቤት ኪራይ ከፍለው ለማስተማር አቅም ስላልነበራቸው እርሱ ራሱን እና ቤተሰቡን ለመርዳት በባሕር ዳር ጎዳናዎች ላይ በጉልበት ሥራ ለመሰማራት ተገድዷል።
በትውልድ ቀዬው ሌላ የሥራ አማራጭ ባለመኖሩ፣ በቀን የሚያገኘው ገቢ ከምግብ እና ከቤት ኪራይ የማይዘል ቢኾንም ይህን አድካሚ ሥራ ለመሥራት መርጧል።
ይህ የሕይወት ፈተና ግን ተስፋውን አላጨለመውም፤ በሥራ ላይ እያለ ያገኘው አንድ ደግ ግለሰብ፣ በትምህርት ፍቅሩ ተነክቶ በራሱ የግል ትምህርት ቤት በነፃ እንዲማር ፈቅዶለታል። በሚቀጥለው ሳምንት ያቋረጠውን ትምህርት ዳግም ሊጀምር ነው።
“እንዲህ ዓይነት አርቆ አሳቢ እና ለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚጨነቅ ሰው በመገኘቱ ደስ ብሎኛል” ሲል በፈገግታ ይናገራል።
የዚህ ታዳጊ ታሪክ የአንድ ግለሰብ ታሪክ ብቻ አይደለም። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ቢመለሱም አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ማራቃቸውን ገልጿል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታዳጊዎች አሁንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ርቀው ለጉልበት ብዝበዛ እና ለሥነ-ልቦና ጫና ተጋልጠዋል። ሴት ተማሪዎች ደግሞ ለያለድሜ ጋብቻ እና ለተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ እየኾኑ ይገኛሉ።
ዛሬ ላይ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ የረቀቁ ሀገራት መሠረታቸው ትምህርት ነው።
ኢትዮጵያም በዕውቀት የዳበረ ትውልድ ያስፈልጋታል ብለን ብናምንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን ከትምህርት ገበታ ውጭ አድርገናል።
ለልጆቻችን የነገ እጣ ፈንታ ስንል ሰላምን መስበክ እና ለፍትሕ መቆም ታሪካዊ ኀላፊነትን መወጣት ነው።
እያንዳንዱ ግለሰብ በያገባኛል ስሜት የልጆችን የመማር መብት ለማስከበር ሊረባረብም ይገባል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleችግርን ተቋቁሞ በወርቅ ሜዳሊያ እና በዋንጫ የደመቀው የቀለም ጉዞ።
Next articleባለፉት ወራት በአማራ ክልል ከ469 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።