ችግርን ተቋቁሞ በወርቅ ሜዳሊያ እና በዋንጫ የደመቀው የቀለም ጉዞ።

11
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በ8ኛ ዙር የምርቃት መርሐ ግብሩ ካስመረቃቸው 497 ተማሪዎች መካከል የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተመራቂዋ ዓባይነሽ ታምር 3 ነጥብ 97 ውጤት በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀች ኮከብ ተማሪ ኾናለች።
ተመራቂዋ ከአጠቃላይ ተመራቂ ተማሪዎች እና ከሴት ተመራቂ ተማሪዎች ከፍተኛ ነጥብ በማምጣትም ሁለት ሜዳሊያ እና ሁለት ዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላታል።
ተመራቂዋ ከአሚኮ ዲጂታል ጋር በነበራት ቆይታ የአርሶ አደር ቤተሰብ ልጅ መኾኗን ተናግራለች። ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ እያለፈች ትምህርቷን እንደተከታተለችም ገልጻለች።
ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የቤተሰቦቿ ድጋፍ ትምህርቷን በስኬት እንድታጠናቅቅ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም ተናግራለች።
በተለይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ለንባብ የሚኾኑ ሰነዶችን ለማባዛት እና ለሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች ገንዘብ ያስፈልጋት እንደነበር ያስታወሰችው ተመራቂዋ ነገር ግን አርሶ አደር ቤተሰቦቿን ላለማስቸገር ስትል ከጓደኞቿ እየተዋሰች ታነብ እንደነበር ገልጻለች።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ እያንዳንዱን ጊዜዋን ለትምህርቷ በመስጠት፤ መምህራን የሚሉትን በአግባቡ በመከታተል፣ በመተግበር እና ቀን ከሌሊት በማንበብ ለውጤት መብቃት እንደቻለች አብራርታለች።
ዩኒቨርሲቲው እና መምህራን ያደርጉት የነበረው ድጋፍ እና ክትትልም ለውጤቷ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተናገረችው።
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ስለተመራቂዋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባጋራው መረጃ ተማሪ ዓባይነሽ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ካሳየችው ጠንካራ የትምህርት ተነሳሽነት ባለፈ ለማኅበረሰቡ ያበረከተችው አስተዋጽኦ የሚደነቅ እንደኾነ ጠቅሷል።
በተለያዩ የኀላፊነት ቦታዎች እና በበጎ አድራጎት ሥራ ላይም የነቃ ተሳትፎ እንደነበራት ገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው ተመራቂዋ ላስመዘገበችው የላቀ ውጤት ዕውቅና ለመስጠት በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት ተቀጥራ እንድታገለግል የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ማጽደቁን በምርቃቷ ዕለት አብስሯል።
ተመራቂዋን ዩኒቨርሲቲው ተቀብሎ ከማስተማሩ ባለፈ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በማድረጉም አመሥግናለች።
ትምህርት ለሰው ልጅ መሠረታዊ ነገር መኾኑን የተናገረችው ተመራቂዋ ታዳጊዎች ለትምህርት ትኩረት እንዲሰጡ አሳስባለች።
በቀጣይ በመምህርነት ዘመኗ እንደእርሷ ውጤታማ ተማሪዎችን ለማፍራት ተግታ እንደምትሠራም ተናግራለች።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበጎንደር ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
Next article“ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎችን ስመለከት እንባ ይተናነቀኛል”