
ባሕርዳር: መጋቢት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። በጎንደር ከተማ ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም በወተት ምርት፣ በዶሮ እርባታ፣ በከብት ማድለብ እና በንብ ማነብ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
በዘርፉ የበለጠ ውጤት ለማምጣት የውኃ፣ የመኖ አቅርቦት፣ የማስፋፊያ ቦታ እና የብድር አቅርቦት ችግሮች እንዳሉባቸው አልሚዎች ያነሳሉ።
የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በመፍታት እና ዘመናዊ አሠራርን በመከተል ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ መላኩ ደምሌ በዘርፉ ምርታማነትን ለመጨመር በዝርያ ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለአልሚዎች ሙያዊ ሥልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ እንደገለጹት የሌማት ቱሩፋት መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው። በወተት ላም እርባታ፣ በከብት ማድለብ እና በንብ ማነብ ዘርፎችም የክላስተር አሠራር ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ይህም የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና ዘመናዊ አሠራርን በመከተል ምርታማነትን ለመጨመር መሠረት ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ከተማ አሥተዳደሩ በ68 ሚሊዮን ብር ወጭ የዶሮ ክላስተር ሸድ ገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባቱን አንስተዋል።
በቀጣይም 139 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ ተጨማሪ ሼዶችን ለመገንባት ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት። በኢንቨስትመንት ደረጃ ማልማትም ለሚፈልጉ ባለሀብቶች መሬት ከመስጠት ጀምሮ የተጠናከረ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ካሉት 199 ኢንተርፕራይዞች መካከልም 156 ለሚኾኑት 480 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲቀርብ ተደርጓል ነው ያሉት። በቀጣይም ይህንን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የመኖ አቅርቦት እና ሌሎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍም ከባለሀብቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
