ወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን አስመረቀ፡፡

24

 

ደሴ: መጋቢት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ በመጀመርያ እና በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በመማር ማስተማር ሥነ ዘዴ ለ18ኛ ጊዜ ያሠለጠናቸውን 1ሺህ 444 ተማሪዎችን አስመርቋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ.ር) በጥሩ የሥነ ምግባር ሙያ ሠልጥናችሁ ለምረቃ የበቃችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ የሠለጠነ የሰው ኀይል ከማፍራት እና ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ በማድረግ በኩል ትልቅ ሥራ ሠርቷል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ። ዩኒቨርሲቲው ለጤና፣ ለቴክኖሎጂ እና ለማኅበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የተማሪ ወላጆች አምናችሁ ልጆቻችሁ በሥነ ምግባር እና በዕውቀት የበለፀጉ እንዲኾኑ ሰጥታችሁ ለዛሬው ቀን በመድረሳቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል::

ተመራቂዎች ሥራ ፈላጊዎች ሳይኾኑ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲኾኑ መልዕክት ያስተላለፉት ዶክተር አወል ሰይድ በየአካባቢያቸው ሲሄዱ ለሀገራቸው ዕድገት እና ለውጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ውድመት ቢደርስበትም ከማኀበረሰቡ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዳግም ወደነበረበት አቋም መመለሱን አንስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ጊዜ በማኀበራዊ እና በምርምር ዘርፉ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነ ነውም ብለዋል።

ከ65 በላይ ማኀበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶች ላይ የማኀበረሰቡን ችግር ከመፍታት አኳያ ዩኒቨርሲቲው እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ ዶክተር አወል በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በመስጠት መምህራን እና ተማሪዎች ወቅቱን ያገናዘበ ዕውቀት እንዲጨብጡ ዩኒቨርሲቲው የራሱን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ተመራቂዎች ለሀገር እና ለሕዝብ አለኝታ መኾን እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት። ተመራቂዎቹ አሁንም መማር ማቋረጥ እንደሌለባቸው አሳስበዋል። “ስኬታችሁን በምታገኙት ሳይኾን በምትሰጡት እየለካችሁ ለምንም ነገር ተስፋ አትቁረጡ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል እና የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባ በመኾኑ ተመራቂዎችም ሀገራቸውን የመገንባት ትልቅ ድርሻ አለባቸው ብለዋል።

ሀገራቸው ከተመራቂዎች ብዙ እንደምትጠብቅም ጠቁመዋል። ከአካዳሚያዊ ዕውቀት ባሻገር የወሎን ማኅበረሰባዊ እሴት ይዘው እንደወጡ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ቴዎድሮስ ፈረደ በምረቃው ሥነ ሥርዓት የተገኙ ሲኾን ይህ ምርቃት የሕይወታቸው ምዕራፍ መጨረሻ ባለመኾኑ መማር ሳያቋርጡ ከዚህ የበለጠ ዕውቀት በመቅሰም ራሳቸውን መለወጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ተመራቂ ተማሪዎችም ማኅበረሰባቸውን በታማኝነት ለማገልገል ቃል ገብተዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በመማር ማስተማር በመደበኛ፣ በማታ እና በድህረ ምረቃ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በምርምር ሀገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ያለ ዩኒቨርሲቲ መኾኑ ተገልጿል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ18 ዓመት ውስጥ 50 ሺህ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለኢትዮጵያ ሕዳሴ የበኩሉን ድርሻ ስለመወጣቱም ተብራርቷል፡፡

በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል ኪሮስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

#አሚኮ #ኢትዮጵያ #አማራ_ክልል #ደሴ #ወሎ #ዜና #ተማሪ #ምረቃ #ሥራ

Previous article“በየሄዳችሁበት የሰላም አምባሳደር ኹኑ” የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ
Next articleምርጫ፣ ሰላም እና ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡