“በየሄዳችሁበት የሰላም አምባሳደር ኹኑ” የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ

8

 

ደሴ: መጋቢት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ መካነሰላም ግቢ ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።

“ከዩኒቨርሲቲው እውቀትና ክህሎትን አግኝታችሁ ዛሬ ለመመረቅ የበቃችሁ ተማሪዎች እንኳን ደስ ያላችሁ” ያሉት የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ መካነሰላም ግቢ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አብዱሮህማን አወል ሳይማር ያስተማራችሁን ማኅበረሰብ በቅንነት እንድታገለግሉ አደራ እላለሁ ብለዋል። በዛሬው እለት በመካነሰላም ግቢ 351 ተማሪዎች መመረቃቸውንም ገልጸዋል።

ዛሬ በደስታ የፈኩ የተመራቂ ፊቶችን ለማየት የቤተሰብ አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደኾነ ያነሱት ዳይሬክተሩ የተመራቂ ቤተሰቦችን እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዩኒቨርሲቲው ቆይታችሁ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፋችሁ ለዚህ በመድረሳችሁ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፋለሁ ብለዋል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ካሳ ሻውል (ዶ.ር)።

ዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ ተቋማት የሪፎርም አጀንዳዎችን እየተገበረ ይገኛል ብለዋል። በዋናነት በዲጂታል ሪፎርም ሰፊ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት 4 ሺህ 268 ተማሪዎችን እያስተማረ ሲኾን በሁለቱም ግቢ 698 ተማሪዎች መመረቃቸውን ተናግረዋል። ከነዚህም ውስጥ 38 ተማሪዎች በሁለተኛ ዲግሪ መመረቃቸውን አውስተዋል።

መማር ከትምህርት ቤት ውጭ በተግባር ሲውል ለሀገር ግንባታ ይውላል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሰላም ለሁሉም መሰረት ነውና በየሄዳችሁበት የሰላም አምባሳደር እንድትኾኑ አደራ እላለሁ ብለዋል።

ዘረኝነትን፣ ጎጠኝነትን እና ከፋፋይነትን የምትፀየፉ ትውልዶች እንድትኾን አደራ እላለሁ ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሁን የምትቀላቀሉት ወደ ትልቁ ዓለም ስለኾነ እውቀታችሁን ለራሳችሁ ብቻ ሳይኾን ለሕዝባችሁ እንድታወሉት አደራ እላላሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየ51 A+ እና የሁለት ዋንጫዎች ባለክብር ሴት ከመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ!