
ጎንደር: መጋቢት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ ጎንደር ከተማን ወክለው ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎችን የማስተዋወቅ መርሐ ግብር አካሂዷል።
ፓርቲው የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤት አባላት እጩዎቹን ነው በጎንደር ከተማ ያስተዋወቀው።
አቶ አገኘሁ ተሻገር እና አቶ ሙሐመድ እድሪስ ጎንደር ከተማን ወክለው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ እጩዎች መኾናቸው ተነግሯል። ወይዘሮ ባንችይርጋ መለሰ፣ ሞላ መልካሙ(ደ.ር)፣ ዘላለም ልጃለም (ዶ.ር) እና አቶ ቻላቸው ዳኘው ደግሞ የክልል ምክር ቤት እጩዎች ኾነው ተዋውቀዋል።
የፓርቲው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤው አገኘሁ ተሻገር የጎንደር ሕዝብ ለሀገራዊ ለውጡ መምጣት ሚናው የጎላ በመኾኑ “ጎንደርን በመወከል መወዳደር የሚያኮራ ነው” ብለዋል።
ጎንደር እንድትለማ እና እንድትለወጥ ብልጽግና እጁን ዘርግቷል ያሉት አቶ አገኘሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፍተኛ በጀት በመመደብ ጎንደር ላይ ልማት እንዲረጋገጥ አድርገዋልም ነው ያሉት።
ጎንደርን ለማልማት እየተካሄደ ያለው ሥራ ቀጣይነት እንዲኖረው ብልጽግና ፓርቲ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
የመራጮችን ምዝገባ ስኬታማ በማድረግ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ እንዲኾን መሥራት እንደሚያስፈልግም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ ከታሪክ ጠባሳዋ እንድትወጣ መሥራት ችሏል ያሉት ደግሞ የክልል ምክር ቤት እጩው እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ናቸው።
የጎንደር አብያተ መንግሥታትን ጨምሮ ጎርጎራ እና መገጭን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ብልጽግና ፓርቲ ቁርጠኛ እንደኾነም በማሳያነት አንስተዋል።
ለጎንደር ከተማ የለውጥ ጉዞ ከተማዋን የወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት እጩዎች ሚናቸው የጎላ ስለመኾኑም አንስተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን ጎንደርን የወከሉ የፓርቲው እጩዎች ከተማዋን ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ኀላፊነት የመሩ እና በተለያዩ እርከኖች ያገለገሉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዕጩዎቹ ከትምህርት ዝግጅት እስከ ኀላፊነት ያላቸው አገልግሎት እና የሥራ ልምድ ለከተማዋ ልማት እና ሰላም መረጋገጥ አጥጋቢ መኾኑንም በትውውቅ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሳ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
