
አዲስ አበባ: መጋቢት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት አጋሮች ድጋፍ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸውን የግብርና ሜካናይዜሽን መሳያዎችን ለክልሎች አሰራጭቷል።
በርክክብ መርሐግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ግብርናችን ከዘልማዳዊ አሠራር ካልወጣ የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ይቸግረናል ብለዋል።
ዓለም ከዛሬ 265 ዓመት በፊት በትራክተር ማረስ የጀመረ ቢኾንም እኛ ግን አሁንም ከበሬ ጫንቃ አልወጣንም፤ ይሄ ሊያሳስበን ይገባል፤ ፈጥኖ ለመውጣትም ትልቅ የቤት ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።
በመኾኑም አርሶ እና አርብቶ አደሮችን የግብርና ሜካናይዜን በማስታጠቅ ድካምን መቀነስ፤ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ከራስ አልፎ ምርት ለገበያ የምናቀርብበትን ሂደት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ለክልሎች የተሰራጩት የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች 63 ትራክተሮች፣ 71 ወኪንግ ትራክተሮች፣ 150 የእህል ማቀነባበሪያ ማሽኖች፣ 4 ባለብዙ ደረጃ እንቁላል መታቀፊያዎች እና የአንድ ደረጃ መፈልፈያ መሳሪያዎች፣ 5 የከርሰ ምድር ውኃ ማውጫ ማሽኖች፣ 460 በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች፣ 15 የመስክ መገልገያ መኪኖች፣ 243 ሞተር ሳይክሎች፣ 980 ዴስክቶፕ እና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ናቸው᎓᎓
መሳሪያዎቹ ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት፣ ከምግብ ሥርዓት ማጠናከሪ ፕሮግራም፣ ከዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም፣ ከበረሃ አንበጣ መከላከል ፕሮጀክት፣ ከልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም እና ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተገዙ እንደኾነም ነው የተገለጸው።
በዚህም ለአማራ ክልል ከኮሪያ መንግሥት ድጋፍ 4 ትራክተሮች፣ 15 ፓወር ቲለር፣ 15 ሩታበር እና ሌሎችም የእርሻ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጎለታል።
በምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም 25 የሩዝ ማቀናባበሪ ማሽን፣ አንድ ባለ ብዙ ደረጃ የእንቁላል መታቀፊያ ማሽን ፣ በዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም 20 ሞተር ሳይክሎች፣ በበረሃ አንበጣ መከላከል ፕሮጀክት 3 ፒክ አፕ መኪኖች እና 30 ሞተር ሳይክሎች፣ በልማታዊ ሴፍትኔ ፕሮግራም 71 በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች፣ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት 6 ትራክቶች ድጋፍ ተደርጎለታል።
ክልሎች የተረከቡትን የግብርና ሜካናይዜሽን መሳያዎችን ለታለመላቸው ዓለማ ብቻ በማዋል ግብርናውን ለማዘመን የሚደረገውን የመንግሥት ትኩረት እና ጥረት በንቃት እንዲደግፉም የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ አደራ ብለዋል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
