ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን አስመረቀ።

17

 

ወልድያ፡ መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለ13ኛ ዙር ተማሪዎችን አስመርቋል።

ዩኒቨርሲቲው በመደበኛ፣ በማታው እና በክረምት መርሐግብር በአንደኛ እና ሁለተኛ ዲግሪ ያሠለጠናቸውን 2ሺህ 388 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 12 ዙር የምረቃ ሂደት ለሀገር ልማት እና ብልጽግና ብቁ የኾኑ በርካታ ምሁራንን አስመርቋል ብለዋል።

የዚህ ዓመት ተመራቂዎችም በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር በቀሰሙት ዕውቀት እና ክህሎት ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ አደራ ብለዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ተመራቂዎች አራት ዓመት እና ከዚያ በላይ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ቆይታ ከመማር ማስተማር ባሻገር ከወልድያ ከተማ እና ከሕዝቧ ጋር ጥብቅ የኾነ ማኅበራዊ ቁርኝት እንደነበራቸው ጠቅሰዋል።

በዚህ ማኅበራዊ ትስስር የወልድያን ሕዝብ እና የወልድያ ከተማን ሰላም ወዳድነት፣ የአብሮነት እና የፍቅር ተምሳሌትነት በተግባር ዐይተው እንዳረጋገጡ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

በመኾኑም ተመራቂዎች ለሥራ በሚሄዱበት ሀገርም ይሁን በትውልድ ቀያቸው ሲመለሱ የወልድያ አምባሳደር እንዲኾኑም አሳስበዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በመማር ማስተማር ሂደት ለሥራ የሚኾን ዕውቀትን፣ በአብሮነት ቆይታቸው ለነገ የሕይወት ልምድን እንደቀሰሙ አስረድተዋል።

ይህን የዕውቀት፣ የክሎት እና የሕይወት ልምድ ስንቅ ራሳቸውን እና ሀገራቸውን ለመቀየር እንደሚጠቀሙበትም ነው ያብራሩት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልሉን የግብር አሠባሠብ ሥርዓት ለማዘመን ከሚያግዙት ሥራዎች አንዱ የፋይናንስ ሥርዓቱን ማዘመን ነው ።
Next article“ባሕርዳር የተፈጥሮ ገጸ በረከት፣ የውበት ተምሳሌት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ