የክልሉን የግብር አሠባሠብ ሥርዓት ለማዘመን ከሚያግዙት ሥራዎች አንዱ የፋይናንስ ሥርዓቱን ማዘመን ነው ።

8

 

ባሕርዳር፡ መጋቢት 12/2018ዓ.ም (አሚኮ) ሳፋሪኮም ኤምፔሳ ኢትዮጵያ ከአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የሳፋሪኮም ኢምፔሳ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጌታቸው መንግሥቴ እና የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ተፈራርመውታል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የክልሉን የግብር አሠባሠብ ሥርዓት ለማዘመን ከሚያግዙት ሥራዎች አንዱ የፋይናንስ ሥርዓቱን ማዘመን እንደኾነ ተናግረዋል። ይህም እውን እንዲኾን ዛሬ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የስምምነት ፊርማ መከናወኑን ነው የጠቀሱት።

የአማራ ክልል መንግሥት የታክስ ሥርዓቱን በማዘመን የታክስ አሠባሠቡ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝ፣ የግብር ከፋዮችን ጊዜ ቆጣቢ፣ የተመቸ እና ባሉበት ኾነው ግብራቸውን እንዲከፍሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በግብር ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ እና የወረቀት ሥራዎችን ለመቀነስም የሚያግዝ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ወደ ተግባር አስገብቷል ነው ያሉት፡፡

ይህ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ እውን እንዲኾን ደግሞ የክፍያ ሥርዓቱን አሳላጭ የኾኑ የፋይናንስ ተቋማት ያስፈልጉታል ብለዋል፡፡

ለዚህም ዛሬ ከሳፋሪኮም ኢምፔሳ ጋር የተደረገው የስምምነት ፊርማ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ነው የገለጹት፡፡ ይህ ስምምነት በታሰበው እና በተያዘው ውል መሠረት ወደ ተግባር እንዲቀየር ቁርጠኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የሳፋሪኮም ኢምፔሳ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ተወካይ ሥራ አሥፈጻሚ ጌታቸው መንግሥቴ ኢምፔሳ ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የፋይናንስ አካታችነትን ለማስተዋወቅ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

አብዛኛው ቦታ የባንክ አገልግሎት ተደራሽ ነው፤ የፋይናንስ አካታችነትን ግን ውስንነቶች ስለሚስተዋሉበት በተለያየ መንገድ ተቋሙ ማረጋገጥ ይፈልጋል ብለዋል። አብዛኛው ማኅበረሰብ በካሽ ክፍያ ላይ የተመሠረተ እንደኾነም አንስተዋል። ተቋሙ ይህን በካሽ ላይ የተመሠረተ የክፍያ ሥርዓትን የሚከተል ማኅበረሰብ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ማምጣት አንዱ አጀንዳው መኾኑንም ገልጸዋል።

ዲጂታል ሥርዓቱ ገቢ ለሚሠበሥቡ ተቋማት እና ለግብር ከፋዩ ማኅበረሰብም ብዙ ፋይዳ ያለው መኾኑን ተናግረዋል። ኢምፔሳ ኢትዮጵያ ደግሞ የዚያ ድልድይ ኾኖ ለመሥራት ዛሬ ከአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ጋር ስምምነት መፈራረሙን ነው ያነሱት። ከዛሬው ፊርማ ሥነ ሥርዓት በኋላ ወደ ተግባር ፈጥኖ ለመግባትም ቅድመ ዝግጅቶች ሲያደረጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በኢምፔሳ ኢትዮጵያ የክፍያዎች ኀላፊ ቸርነት ገረመው ደግሞ የስምምነቱ መፈረምን አስመልክቶ ሁለቱ ተቋማት ላለፉት ጥቂት ወራት በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። የስምምነቱ መሠረታዊ ነገር በመንግሥት የተቀመጠውን የዲጂታል ኢትዮጵያ 20/30 አቅጣጫ ላይ አስተዋጽዖ ለማበርከት እንደሚያስችል አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወንጀል ምርመራ ሥራ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ መሠረት ነው።
Next articleወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን አስመረቀ።