
ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የሹዋሊድ በዓል ሰላምን፣ አብሮነትን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ እንደሚከበር የሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከቀናት በኋላ የሚከበረው የዘንድሮው የሹዋሊድ ክብረ በዓልን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው የሹዋሊድ ክብረ በዓል በሀረሪ ብሔረሰብ ዘንድ ለምዕተ ዓመታት ሲከበር የኖረ እና በትውልድ ቅብብሎሽ ባሕሉን እና ወጉን ጠብቆ ከነክብሩ ዛሬ ላይ የደረሰ ባሕላዊ በዓል ነው።
የሀረሪ ሕዝብ ልዩ መገለጫ እሴት የኾነው የሹዋሊድ በዓል ከበዓልነቱ ባሻገር የሀረሪ ሕዝብ ጥልቅ የኾነ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እሴቶች መገለጫም ነው ብሏል።
የበዓሉ አከባበር የኢትዮጵያን ሕዝቦች የአብሮነት ዕሴትን እያጎለበቱ ከሚገኙ ባሕላዊ በዓላት መካከል አንዱ መኾኑን ገልጿል። በተለይም በምሥራቁ ኢትዮጵያ ክፍል የባሕል ትውውቅ በመፍጠር የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር በማጠናከር በኩልም ገንቢ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያለው።
የሹዋሊድ በዓል አከባበር ከኅዳር 25/2016 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስ ኾኖ መመዝገቡንም አስታውሷል።
በዓሉ የሀረሪ ሕዝብ ብቻ ሳይኾን የመላ ኢትዮጵያውያን ከዚያም አልፎ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ሃብት ኾኗል ብሏል። ሹዋሊድ በተለይም የክልሉን እና የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲጎለብት በማድረግ የላቀ ጠቀሜታ ያለው በዓልም ነው።
ዘንድሮ የሚከበረው የሹዋሊድ በዓል “ሹዋሊድ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን እና ለቱሪዝም እድገታችን” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበርም ተገልጿል።
ከሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በበዓሉ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና አጎራባች ክልሎች በሀረር ከተማ የባሕል ፌሲቲቫል እና አውደ ርዕይ፣ የልማት ሥራዎች ጉብኝትን ጨምሮ ሌሎች መርሐ ግብሮች ይካሄዳሉ ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
