
ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ጋር “በመደመር መንግሥት እይታ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ሚና” በሚል መሪ መልዕክት የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብራና ፍቃ፤ ፊደል ቀርጻ እና ታረክ ጽፋ ሀገር በማስቀጠል እና በማጽናት ትልቅ ድርሻ ያላት ናት ብለዋል። በታሪክ ውስጥም ከፍ ያለ ቦታ እንዳላት ገልጸዋል።
የሃይማኖት ተቋማት የሀገር ግንባታ ምሰሶ ናቸው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ቤተክርስቲያኗ ሀገር ችግር፣ ጦርነት እና ግጭት በገጠማት ጊዜ በጸሎት እና በማሥተባበር ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የድርሻዋን ስትወጣ ቆይታለች ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች የቀደመውን እና አሁን ያለውን ታረክ በእውነት ላይ ተመስሮቶ ሳይዛባ ለትውልድ ማስቀጠል እንደሚገባቸውም አንስተዋል። መንግሥት እና ሃይማኖት የማይነጣጠሉ በመኾናቸው የሃይማኖት አባቶች በባለቤትነት ሀገር እንድትጸና ለሰላም መሥራት አለባቸው ነው ያሉት። ለሀገር ሲባል አንድ ኾነን ተባብረን መሥራት እና የልማትን ሥራዎችን ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገር ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሰላምን፣ ፍቅርን እና አንድነትን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል።
ሰላም ለሁላችሁ ይሁን ተብሎ በአስተምህሮ እንደተነገርው በምድር ላይ ትልቁ ሀብት ሰላም እንደኾነም ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች ሁልጊዜ ለምዕመናን እና ለተከታዮች ሰላምን ማስተማር ይገባቸዋል ነው ያሉት። ሰላም እናት ናት፤ ሰላም ለሁሉም ናት፣ ያለ ሰላም መኖር ስለማይቻል የድርሻችን እንወጣለን፤ ከልማት ሥራዎች ጎንም መሰለፍ ይገባናል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅ መላከ ሰላም ላዕለም ጌታሁን ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰላም አጽንኦት ሰጥታ ታስተምራለች ነው ያሉት። ሰላምን በመስበክ፤ ግብረ ገብነትን በማስተማር እና በማስረዳት የሰላም እሴቶቹን ማጎልበት እና በሀገር ግንባታ የበኩልን መወጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶች የሰላም እሴትን ከመገንባት አንጻር የሚጫወቱትን ሚና ተገንዝበው የሚከተላቸውን ምዕመን የማስተማር እና የመምከር ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።
ዘጋቢ: ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
