ጋዜጠኞች ለብሔራዊ ጥቅም በኀላፊነት ሊሠሩ ይገባል።

6

 

አዲስ አበባ: መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሚዲያ ባለሙያዎች ለብሔራዊ ጥቅም ሲባል የዘገባ ሥራዎችን በኀላፊነት ሊጠቀሙ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አሳሰበ።

ባለሥልጣኑ የመጀመሪያው ዙር የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩ ጋዜጠኞችን አስመርቋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ዘርፉ በብዙ ውጣውረድ ያለፈ እንደመኾኑ የሚታዩ ግድፈቶችን ለመቅረፍ የተደራጀ የልህቀት ማዕከል በማቋቋም የአቅም ግንባታ ተግባራትን እየሠራ ነው ብለዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎች በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ዕውቀት ኖሯቸው ማኅበረሰቡን እንዲያነቁ አስቻይ ሥልጠና መሰጠቱንም ተናግረዋል። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሲባል በዘገባ ሥራዎች ተአማኒ መረጃን ማድረስ ይጠበቃል ነው ያሉት።

እንደ ሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጠናከርም ዘገባዎችን በኀላፊነት መሥራት እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ሠብሣቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መሠረታዊ ሃሳብ፤ ክህሎት እና ተግባቦት የሥልጠናው አላማ መኾኑን ገልጸዋል። የሚዲያ ባለሙያዎች የያዙት መሣሪያ ሀገርን የመኮትኮት እና የማጥፋት አቅም እንዳለው ተረድተው የተደላደለች ሀገርን ለመፍጠር ሕግ እና ሥርዓትን ተከትለው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

ሀገርን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት በቂ የዘርፍ ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች ማሠልጠን አጋዥ መኾኑንም አንስተዋል። ተጨማሪ ዕውቀቶችን በተለያዩ መስኮች መስጠት የሚያስችለው ሥልጠና ቀጣይነት እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

ዛሬ የተመረቁት ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ 36 ባለሙያዎች መኾናቸው ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ቤተልሔም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም እናንተን የሚቀበለው በያዛችሁት ዲግሪ ብቻ ሳይኾን በምትፈጥሩት ለውጥ ጭምር ነው።
Next articleየሚታይ ውጤት በማስመዝገብ የተግባር ሰው መኾን ይገባል።