ዓለም እናንተን የሚቀበለው በያዛችሁት ዲግሪ ብቻ ሳይኾን በምትፈጥሩት ለውጥ ጭምር ነው።

6

 

ደብረ ብርሃን: መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 1 ሺህ 08 ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ለ19ኛ ጊዜ ነው በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት እና በርቀት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ተማሪዎችን እያስመረቀ የሚገኘው።

ከተመራቂዎቹ መካከል 919ኙ በመጀመሪያ ዲግሪ፤ 87ቱ በሁለተኛ ዲግሪ እና ሁለት ተማሪዎች ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማረ መለሰ (ዶ.ር) ተቋሙ የተግባር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በመኾኑ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ለሀገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል። ተማሪዎች የንድፈ ሀሳብ ትምህርትን በተግባር እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ደግፈው ዕውቀት እንዲያዳብሩ መደረጉንም ገልጸዋል።

ተመራቂዎች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለሀገር እድገት እና ለሰው ልጆች ደኅንነት እንዲተጉ አሳስበዋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ አባል አበበ ባልቻ ተመራቂዎች ሥራ ጠባቂ ሳይኾኑ ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ አስገንዝበዋል። ዓለም እናንተን የሚቀበለው በያዛችሁት ዲግሪ ብቻ ሳይኾን በምትፈጥሩት ለውጥ ጭምር ነው ብለዋል።

ተመራቂዎች በማንኛውም ሁኔታ አቋራጭ መንገድን ሳይመርጡ በታታሪነት እና በሥነ ምግባር የታነጸ ሕይወት እንዲመሩም አስገንዝበዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 19 ዓመታት ውጤታማ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን እና ወደፊትም ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን በማሳደግ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ ወደ ልህቀት የሚያደርገውን ጉዞ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ዘጋቢ: ደጄኔ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሌማት ቱርፋት መርሐ ግብር ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ ነው።
Next articleጋዜጠኞች ለብሔራዊ ጥቅም በኀላፊነት ሊሠሩ ይገባል።