ነዳጅን በጥቁር ገበያ ለማዘዋወር መሞከር ጥብቅ እርምጃ ያስወስዳል።

5

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የነዳጅ እጥረት እንዳይከሰት እና ይህንን ችግር ለመሻገር እንደ ሀገር ያለውን የነዳጅ ክምችት ሁሉም ዜጋ በቁጠባ እና በኀላፊነት እንዲጠቀም መመሪያ መተላለፉ ይታወሳል። ከዚህ ጋር በተያያዘም በአማራ ክልል ነዳጅን በቁጠባ እና ወሳኝ ለኾኑ ጉዳዮች ብቻ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው።

ክልሉ ተግባሩን ለማስፈጸም የተለያዩ ስልቶችን እና ስምሪቶችን ሰጥቶ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ እየሠራም ይገኛል።

የአማራ ክልል መንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ የመንገድ ደኅንነት ትራንስፖርት ክትትል እና ቁጥጥር ዳይሬክተሩ ደሳለኝ አዳነ የነዳጅ ጉዳይ በጥብቅ ዲሲፕሊን መመራት የሚያስፈልገው በመኾኑ የሚመለከታቸው አካላት በሁለት መድረክ እንዲመክሩ እና ተግባሩን እንዲወስዱ ስለመደረጉ ገልጸዋል።

ከባሕር ዳር መናኽሪያ ጀምሮ በክልሉ የትራንስፖርት ማኅበራት እና ባለሃብቶች ድረስ ነዳጅን በቁጠባ የሚጠቀሙበት ሁኔታ እንዲፈጠር መግባባት ላይ መደረሱንም ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል።

በተለይም ተሽከርካሪዎችን ከሳልቫቲዮ በላይ አሠርቶ ከነዳጅ ማደያ የመቅዳት ሁኔታ እንዳይኖር ቁጥጥር እንደሚደረግ ሁሉም እንዲገነዘብ ተደርጓል ብለዋል።

የነዳጅ እጥረቱን ሊያባብስ ከሚችለው የጥቁር ገበያ ሁሉም ዜጋ እንዲታቀብ ጥብቅ መመሪያ እንደተላለፈ ገልጸዋል። በዚህ ተግባር ላይ በተገኙት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወሰድም አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ነዳጅን ቀድተው ወደ ሥራ ያልገቡትን እየለዩ እርምጃ በመውሰድ ወደ ሥራ የማስገባት ተግባር እየተፈጸመ መሆኑን ጠቁመዋል።

የነዳጅ እጥረት አለ በሚል የተዛባ መረጃ መንግሥት ካወጣው ታሪፍ በላይ የሚያስከፍል እና ትርፍ የሚጭኑት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል።

በሰባት የክልሉ ዞኖች እና በሰባት ሪጅኦፖሊታንት ከተሞች ስምሪት ተሰጥቶ የነዳጅ እጥረት የሚፈጥሩት ላይ ክትትል እንዲያደርጉ መደረጉንም አብራርተዋል።

የመንግሥት ተሽከርካሪዎችም ቢኾኑ መሪዎች በተቋሙ ለሚከወኑ አስፈላጊ ለኾኑ ሥራዎች ብቻ ነዳጅ እንዲጠቀሙ እንዲያደርጉ ስለመደረጉ እና ይህም እስካሁን በጥብቅ ዲስፕሊን እየተመራ ስለመኾኑ ገልጸዋል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚዋጋው ሀገርን ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት ከሚባዝኑ ጠላቶች ጋር ነው” ለኦፕሬሽናል ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ