
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 447ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በጎንደር ከተማ ተከብሯል።
የዒድ አልፈጥር በዓል በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንደኛው ነው። በበዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱም ባለፈ ማኅበራዊ መስተጋብር ጎልቶ ይታይበታል።
የጎንደር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት እና የከተማ አሥተዳደሩ ዑለማ ምክር ቤት ሠብሣቢ ሀጂ ሼህ ኢብራሂም ሙሃመድ ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥር በዓልን ሰላምን እና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ ሊያከብረው እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር ከተማ የመቻቻል እና የአብሮነት ከተማ ናት ብለዋል።
የሃይማኖት ብዝኃነትን ለዘመናት ጠብቃ የኖረች ከተማ መኾኗን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም ጎንደር ከተማ የአብሮነት እና የመቻቻል ተምሳሌት መኾኗን ተናግረዋል። የዒድ አልፈጥር በዓል የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴቶች ጎልተው የሚከናወኑበት ሃይማኖታዊ በዓል ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አዲሱ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
