
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በግብርና አቅርቦት እና አገልግሎት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው።
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ የሺመቤት ነጋሽ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ 35 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬት፣ ከ224 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የውኃ ሃብት እና ሰፊ አምራች የሰው ኃይል ያላት ሀገር መኾኗን በዕለቱ አንስተዋል።
ግብርናው በኢትዮጵያ የ32 በመቶ የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ምንጭ ከመኾኑ ባለፈ 50 በመቶ የሚኾነውን የውጭ ምንዛሬ የሚሸፍን ነውም ብለዋል። እነዚህን ጸጋዎች ተጠቅሞ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ዋነኛ ግብ መኾኑንም አስረድተዋል።
ኮርፖሬሽኑ በ2008 ዓ.ም ሲቋቋም የግብርና ምርት አቅራቢ፣ የሜካናይዜሽን አገልግሎት እና ቴክኒክ እንዲሁም የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦትን ጨምሮ አምስት ድርጅቶችን በማቀናጀት ግብርናውን ለማዘመን እና የግብዓት እሴት ሰንሰለትን ተደራሽ ለማድረግ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ የሀገሪቱን 30 በመቶ የምርጥ ዘር አቅርቦት ፍላጎት እየሸፈነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የግብርና ግብዓትን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለደንበኞች ለማድረስ እና ደንበኛው ወደ ተቋሙ እንዲመጣ ከመጠበቅ ይልቅ ተቋሙ ወደ ደንበኛው በመቅረብ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የሀገሪቱን የፖሊሲ ስትራቴጂ ተከትሎ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት በተለይ የዘይት ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚረዱ እንደ አኩሪ አተር እና ሱፍ ያሉ ግብዓቶችን ከማባዛት አኳያ አዳዲስ እሳቤዎችን ይዞ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ነው ሥራ አሥፈጻሚዋ የገለጹት።
ይህ የምክክር መድረክም በዋናነት እንደ ሀገር በዘርፉ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በሚያስችሉ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ለመምከር ያለመ መኾኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የክልሉን ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ገዝቶ በማቅረብ፣ ምርጥ ዘሮችን በማባዛት እና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ የክልሉን ግብርና ለማዘመን የማይተካ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ግዙፍ የመንግሥት የልማት ተቋም እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ክልሉ የግብርናውን ዘርፍ በቀጣይ አሥር ዓመታት ውስጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል የ10 ዓመት የግብርና ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱንም ዶክተር ድረስ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
