የመረዳዳት እና የመተሳሰብ እሴቶችን በማጠናከር በዓሉን በጋራ ማክበር ይገባል፡፡

9
ሁመራ፡ መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 447ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሁመራ ከተማ ተከብሯል።
አሚኮ ካነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች የረመዳን ወር ልዩ መኾኑን ገልጸዋል። ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ሃይማኖቱ የሚያዝዘውን መልካም ነገር በሙሉ በመፈፀም ሊኾን ይገባል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ በዞኑ ያለውን ሰላም በማስጠበቅ ለሰላም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በመወጣት በዓሉን እንደሚያከብሩም ጠቁመዋል።
የዚህን ዓመት የዒድ-አልፈጥር በዓል ልዩ የሚያደርገው ለዘመናት ስናነሳው የነበረው የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ፈር የያዘበት ወቅት በመኾኑ ነው ያሉት ደግሞ የሰቲት ሁመራ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሐጅ ጣሂር አብዱልለጢፋ ናቸው፡፡
በቀጣይም መጭውን ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ በማድረግ ጥያቄዎቻችን በዘላቂነት እንዲፈቱ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሰቲት ሁመራ ከተማ ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ ጾሙ ሕዝበ ሙስሊሙ ከፈጣሪው ጋር የተገናኘበት እና ለወገኖቹ እዝነትን ያደረገበት ነው ብለዋል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ ረመዷን አልቆ ዒድ አል ፈጥርን ሲያከብርም በጾሙ ወቅት ያሳየውን መተሳሰብ እና መደጋገፍ ማስቀጠል እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡
የዒድ አል ፈጥር በዓል ክፋት እና ጥላቻ በይቅርታ የሚሻሩበት ነው ያሉት ከንቲባው መልካምነት፣ እዝነት እና መተሳሰብ ደግሞ ከፍ ብለው የሚታዩበት መኾኑን አንስተዋል፡፡
በዓሉን ስናከብር ለክልላችን እና ለአካባቢያችን ሰላም በጋራ በመቆም፤ ምርጫው ስኬታማ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በመሥራት ሊኾን ይገባል ነው ያሉት፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ የመረዳዳት እና የመተሳሰብ እሴቶችን በማጠናከር በዓሉን በጋራ ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ የዞኑን ሰላም እና ልማት ለማስቀጠል የሚያደርገውን ድጋፍ እና ጥረት ያደነቁት ኀላፊው ይህንን አጠናክሮ ማዝለቅ ተገቢ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
በጾም ወቅት የተስተዋለውን መተሳሰብ፣ መደጋገፍ እና መረዳዳት ባሕል አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
Previous articleለሰላም አንድ ኾኖ መሥራት ይገባል።
Next articleለሀገር አንድነት በአብሮነት መሥራት ይገባል።