“የጀነት ሴት” የተባሉት ኡም አይመን በዒድ በዓል ሲታወሱ።

23

 

ባሕርዳር፡ መጋቢት 11/2018ዓ.ም (አሚኮ) የዒድ አል ፈጥር በዓል የጾም መጠናቀቂያ እና የምሥጋና በዓል ነው። በዚህ ልዩ ወቅት አንዲት እናትን ልናስታውስ ወደድን። ኡም አይመን ይባላሉ። የኡም አይመን የመጀመሪያ ሙሉ ስማቸውም በረካ ቢንት ሳዕላባ አል ሀበሺ ነው። ከሀበሻ የሚወለዱ ሀበሻዊት ሴት ናቸው።

ኡም አይመን (የአይመን እናት) የሚለው መጠሪያ የተሰጣቸው አይመን የተባለውን የመጀመሪያ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ የወጣላቸው ስም እንደኾነ ይነገራል። ኡም አይመን ነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ከልጅነታቸው ጀምሮ ልክ እንደ እናት ኾነው ያሳደጓቸው ናቸው።

አቅፈው እና ተንከባክበው እንደ ልጃቸው ፍቅር ሰጥተዋቸዋል። የእናትነት ፍቅርን ለግሰው፤ አገልጋይ ኾነው ለነብያቸው ታምነዋል። የሃይማኖታቸውን ፍሬም በሕይወታቸው አሳይተዋል። የጀነት ሰው መኾናቸውንም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መስክረውላቸዋል።

ኡም አይመን እስልምናን ቀድመው ከተቀበሉ ሴቶች መካከልም አንዷ ናቸው። በጦርነት ታሪክም አላቸው። ልጃቸውን እና ባለቤታቸውን ያጡትም በጦርነት ነበር።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም እንዳብራሩት እሙ አይመን ነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ከልጅነታቸው ጀምሮ እየተንከባከቡ ያሳደጉ እና የእናትነት ሚናን የተወጡ እናት ናቸው። ነብዩ ሙሐመድም (ሰ.ዐ.ወ) ሁለተኛዋ እናቴ ይሏቸው እንደነበር ያስረዳሉ።

የዒድ አል ፈጥር በዓል እና ኡም አይመን ያላቸው ታሪካዊ ትስስር ከመጀመሪያው የዒድ በዓል ጀምሮ እንደኾነ ይነገራል። ኡም አይመን በዚህ በዓል በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ቤት ውስጥ እንደ እናት የሚታዩ ታላቅ ባለውለታ ነበሩ።

በበዓል ቀን የሚታየው የቤተሰብ ዝምድናን የማጠናከር እና ታላላቆችን የመዘየር ተግባር በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ትልቅ ስፍራ ነበረው። በመጀመሪያው የዒድ በዓልም ኡም አይመን በቤታቸው ውስጥ እንደ ዋነኛ የቤተሰብ አባል ኾነው አክብረዋል። ኡም አይመንን ሲዘይሩም “የኡማ” (እናቴ) ብለው በመጥራት እና ልዩ ክብር በመስጠት እንደነበር ሼህ ሙሐመድ ያስረዳሉ።

በዓሉ በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ቤት ሲከበር ኡም አይመን ከመዲና ሴቶች ጋር በመኾን የደስታቸው ዋነኛ ተካፋይ ነበሩ ይላሉ። በበዓሉ ወቅት ነቢዩ ለቤተሰቦቻቸው የሚሰጡት እንክብካቤ የሚጀምረው በኡም አይመን የቤተሰባዊ ፍቅር እንደነበርም ጠቁመዋል። የመጀመሪያው የዒድ በዓል ዝግጅት እጅግ አስደሳች እና አዲስ እንደነበርም አስረድተዋል።

ሼህ ሙሐመድ እንዳሉት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በልጅነታቸው ወላጆቻቸውን አጥተው በኡም አይመን እጅ ሲያድጉ ያደረጉላቸውን እንክብካቤ ስለሚያውቁ በዒድ ቀን ጨዋታ ከሌሎች ሀበሻ ሴቶች ጋር እንዲጫወቱ ፈቅደውላቸዋል።

ከሸክላ የተሠራች አታሞ እየመቱ ሴቶች ለብቻቸው ኾነው በደስታ ይጫወቱ እንደነበር እና በዚህም ከነብያችን ፊት እንዲህ ትጫወታላችሁ? ብለው ሰሐቦች ሲቆጧቸውም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) “ተዋቸው ዛሬ እኮ ዒድ ነው ሴቶች ብቻቸውን ኾነው ይጫወቱ” በማለት ፈቅደውላቸዋል ብለዋል።

ይህ ታሪካዊ ክስተት በበዓል ቀን የሚታየውን የቤተሰብ ፍቅር የሚያሳይ ህያው ተምሳሌት ኾኖ ዘልቋልም ይላሉ።

በአሁኑ ወቅትም ከእነ ኡም አይመን በመማር የዒድ በዓል ሲከበር በእስልምና ሃይማኖት ሥርዓት መሠረት ሴቶች ከወንዶች ጋር ሳይቀላቀሉ ለብቻቸው መጫወት እንደሚችሉ እና ዘና ብለው በዓሉን ማሳለፍ እንደሚገባ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም ይመክራሉ።

ዒድ ሙባረክ!!!

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

  1. ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ከታመኑት የታመነች፤ የእውነት ምድር የተባለች”
Next articleለሰላም አንድ ኾኖ መሥራት ይገባል።