“ከታመኑት የታመነች፤ የእውነት ምድር የተባለች”

17

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እርሷ በቃል ኪዳን የተጠበቀች፤ በበረከት የኖረች፤ በደጋጎች የተወደደች፤ በጀግኖች የታጠረች፤ በብልሆች የተመላች፤ ፍትሕ የሚያውቁትን የወለደች፤ ፍትሕ የሚያውቁትንም ስታነግሥ የኖረች፤ በፍቅር እና በጥበብ የሾመች፣ በነጻነት እና በአንድነት የኖረች ናት።

እርሷ አስቀድማ ተመርጣለች፤ በክፉ ዘመን ማረፊያ እና መጠጊያ ኾናለች፤ ከታመኑት ታምናለች፤ ከተወደዱት ሁሉ ልቃ ተወድዳለች። የደከሙት አርፈውባታል፤ የተገፉት ተደግፈውባታል፤ ፍትሕ ያጡት ፍትሕን አግኝተውባታል፤ የተሳደዱት አርፈውባታል፤ መጠጊያ ቤታቸው፤ ማረፊያ እልፍኛቸው፤ መመኪያ ጋሻቸው፤ የክፉ ቀን ምርኩዛቸው አድርገዋታል ኢትዮጵያ።

እርሷ የገነነው ስሟ በታሪክ መዛግብት፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቧል። ስለ ቃል ኪዳን ምድርነቷ፤ ስለ ሰላም እና ፍትሕ አብነቷ፤ ስለ ሃይማኖት ቤትነቷ ተመስክሮላታል።

እርሷን የወደዷት ምድራዊ ነገሥታት፤ መኳንንት እና መሳፍንት ብቻ አይደሉም፤ ደጋጎቹ፣ አምላክ የመረጣቸው የሰማይ ባለሟሎችም ናቸው እንጂ።

ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እርሷን ወድደዋታል፤ መርጠዋታል፤ በክፉ ቀን መጠጊያ ትኾን ዘንድ ተማምነውባታል፤ የፍትሕ እና የርህራሄ ሀገር መኾኗን መስክረውባታል፤ ተከታዮቻቸውንም ሂዱ ወደ ሀበሻ ምድር ወደ ኢትዮጵያ ብለው ልከውባታል፤ እንዳሏትም፣ እንደ መረጧትም ለመልዕከተኞቻቸው የተመቸች፤ ቃል ኪዳኗንም የጠበቀች ሀገር ናት ኢትዮጵያ።

ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለታመኑላቸው ያመኗት፤ በአላህ ለተመረጡት የመረጧት፤ የፍትሕ፣ የሰላም እና የፍቅር ሀገር ያሏት ኢትዮጵያ ሰው ሁሉ እንዳይነካት ቃል ኪዳን ያኖሩላት፤ አብዝተውም የወደዷት ናት።

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ኢትዮጵያን ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተወደደች ናት ይሏታል። ከነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስቀድሞ ቁጥራቸው የበዛ ነብያት እና መልዕክተኞች ተልከዋል፤ እንደ እርሳቸው ግን የኾነ የለም፤ እርሳቸው ለዓለም የበቁ፤ አላህ ያለፈውን፤ የነበሩበትን እና የሚመጣውን ዘመን እንዲያውቁ አደረጋቸው ይላሉ።

አላህ መልዕክተኛውን ጅብሪልን ያዘዘላቸው፤ ጅብሪልም የሚጠብቃቸው ናቸው፤ የሰማይ አባታቸው አላህ የመረጣቸው ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የምድር እናት እና አባታቸውን ያጡት በልጅነት ዘመናቸው ነበር። አባታቸውን ያጡ በተረገዙ ጊዜ ነበር። እናታቸውንም ያጡት ደግሞ ገና በስድስት ዓመታቸው ነበር ይላሉ።

ታዲያ ወላጆቻቸውን ባጡ ጊዜ የሚያቅፏቸው፤ የሚያለብሷቸው እና የሚያጎርሷቸው የአደራ እናት ኾነው የተሰጧቸው ሀበሻዊቷ እናት በረካ ( እሙ አይነመን) ነበሩ። የኢትዮጵያ እና የእስልምና ጥብቅ ትስስርም እዚህ ላይ ይጀምራል ነው የሚሉት።

አላህ የመረጣቸውን ነብይ በረካ ያሳድጉ ዘንድ አደራ ተሰጣቸው። የነብዩ እናት ለሀበሻዊቷ በረካ አደራ ሲሰጡ አደራሽን ልጄን እናትም፤ አባትም፣ ወኪልም ኾነሽ አሳድጊው አሏቸው። በረካም የተቀበሉትን አደራ ሳያጓድሉ ፈጸሙ።

ታላቁን ነብይ በማሳደግ እና በመንከባከብ የሀበሾች ሚና ነበረበት ነው የሚሉት። ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጊዜው በደረሰ ጊዜ ከአላህ የተሰጣቸውን እውነት ገለጡ። በዚያን ጊዜ የእርሳቸው እውነት የገባቸው በአስተምህሯቸው አመኑ። ሌሎች ደግሞ በጠላትነት ተነሱባቸው።

ታማኙ፣ ፍትሐዊው እና ሐቀኛው ሲሏቸው የነበሩ ሁሉ አንድ ጌታ አላህን ብቻ አምልኩ፤ ጣዖታትን ተው ባሉ ጊዜ ጠላት ኾኗቸው። እርሳቸውን እና ተከታዮቻቸውን ያሳድዷቸው ጀመር። በዚያም ጊዜ ተከታዮቻቸውን በዚህ ያለው ችግር እስኪስተካከል ድረስ ፍትሕ እና ሐቅ ወደ አለባት ሀገር ሂዱ አሏቸው።

ተከታዮቻቸውም በዚህ ጊዜ ፍትሕ እና ሐቅ ያለባት ሀገር ከወዴየት ትገኛለች? አሉ። በዚያ ዘመን ፍትሕ ርቃ፤ ሐቅም መንምና ነበርና ነው የሚሉት።

እርሳቸውም ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ። በዚያች ምድር ፍትሕ እና ሐቅ አለ አሏቸው። ወደ ሐቀኛዋ ምድርም ገሰገሱ። በሐበሻ ምድር በኢትዮጵያም ንጉሥ አርማህ የተባሉ ፍትሕ አዋቂ፣ ደግ እና ጀግና ንጉሥ በዙፋኑ ላይ ተቀምጠው ነበር።

ንጉሥ አርማህ (ነጃሺ) የነብዩ መልዕክተኞች በመጡ ጊዜ በፍቅር እና በአክብሮት ተቀበሏቸው። የልባቸውንም መሻት ፈጸሙላቸው። እውነትም ፍትሕ እና ሐቅ አገኙ። የነብዩ ተከታዮች ወደ ሐበሻ ምድር መሄዳቸውን የሰሙ አሳዳጆች ግን ዝም ብለው አልተኙም። ይልቅስ ከንጉሥ አርማህ (ነጃሺ) ዘንድ መጥተው የነብዩን ተከታዮች አሳልፈው ይሰጧቸው ዘንድ ጠየቋቸው። በነብዩ ተከታዮች ላይም የሀሰት ክስ መሠረቱ። ይህን የተመለከቱት ንጉሥ አርማህ እውነታውን ከተከታዮች ዘንድ ጠየቁ። ባወቁም ጊዜ በሀሰተኛ ክስ የከሰሷቸውን ከሳሾች አባረሩ። የነብዩን መልዕክተኞችም በሰላም እና በደስታ ይኖሩ ዘንድ አደረጉ። አደራቸውን እና ቃላቸውንም ጠበቁ።

የሐበሻ ምድር እንደ ሀገር፤ ንጉሥ አርማህ እንደ ንጉሥ ታላቁን ውለታ ዋሉት። ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የሐቀኞችን ምድር እና ሐቀኛውን ንጉሥ ወደዷቸው። እርሳቸውም የሐበሻን ምድር እንዳትነኩ ሲሉ የጠበቀች ቃላቸውን ሰጡ።

ነብዩ መልዕክተኞቻቸውን የሚልኩበት ከኢትዮጵያ የሚቀርቡ ሀገራት ነበሩላቸው። ነገር ግን እንደ እርሷ ፍትሕ ያለባት፤ ሐቅ የመላባት እና የእውነተኛ ምድር አላገኙምና ወደ እውነተኛይቱ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ላኳቸው። ኢትዮጵያም የታላቁን ነብይ መልዕክተኞች ጠበቀች፤ ከእውነቷ ሳትጎድል፤ ከተባለችው ሳትዛነፍ ቃል ኪዳኗን አከበረች።

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የቢሊዮን ሙስሊሞች ባለውለታ ናት፤ የዓለም ሙስሊሞች የኢትዮጵያ እዳ አለባቸው ይላሉ ፕሮፌሰሩ። ስለ ምን ቢሉ ዛሬ ላይ ቢሊዮኖች ከመኾናቸው አስቀድሞ በዚያ ዘመን እውነቱን የተረዱትን፤ በሃይማኖቱ የጸኑትን ተከታዮች ተቀብላለች፤ የነብዩን የአደራ ቃል አክብራለችና።

ኢትዮጵያውያን ይሄን ታላቅ ታሪክ ሊያውቁት ይገባል፤ ይህ ገናና ነውና ነው የሚሉት። ኢትዮጵያ የሐቀኞች እና የፍትሕ ምድር ናት። ለዚህ ደግሞ ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን በሐቅ እና በፍትሕ ጠብቋት፤ በአንድነት እና በፍቅር ከልሏት እንዳሉ ነብዩ እርሷን አትንኳት፤ እርሷን የነኳት ወድቀዋልና። እርሷን ያከበሯት ግን ከብረዋል፤ እርሷን የጠበቋት ተጠብቀዋል፤ በተድላና በደስታም ኖረዋል።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም ምድር የተባለች ሀገር ስለ ምን የሰላም ምድርነቷ ይቅር ?
Next article“የጀነት ሴት” የተባሉት ኡም አይመን በዒድ በዓል ሲታወሱ።