የሰላም ምድር የተባለች ሀገር ስለ ምን የሰላም ምድርነቷ ይቅር ?

15

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ ሰላም ብዙ ተብሏል፤ ዳሩ ግን ሰላም የቃል ሳይኾን የመኾን ፍሬ ነው፡፡ ሰላም አፋዊ ሳይኾን ልባዊ ነው፡፡ ሰላም ምስጢራዊ ሳይኾን ይልቁንም ገሃዳዊ ነው፡፡

ሼህ አሕመድ አወል ሀሰን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የመጅሊስ ዋና ሠብሣቢ ናቸው። የእስልምና ዋና ስብከት ሰላም መኾን ነው ይላሉ። የእስልምና አስተምህሮ ለሰው ብቻ ሳይኾን በምድር ላይ ላሉ ፍጡራን ሁሉ ሰላም እንድንሰጣቸው ያትታል ነው ያሉት።

አላህ ሁልጊዜም ፍትሐዊ ነው ያሉት ሠብሣቢው ከፍትሕ ማፈንገጥን እስልምና ሁሌም አጥብቆ ይቃወማል ብለዋል።

ሰው ለራሱ የሚወደውን ሁሉ ለሌሎችም እንዲያደርግላቸው ያዛል፤ በራሱ ላይ ቢደረግ የማይፈልገውን በሌሎች ላይ እንዲደረግ የሚፈልግ ግን ከአላህ የተጣላ ነው ይላሉ።

ለመጭው ትውልድም አርዓያ የሚኾኑ መልካም ሥራዎችን እየተከሉ መሄድን እንጅ ሳንካን ለቀጣይ ትውልድ ተክሎ መሄድን አስተምህሮው ይቃወማል ብለዋል። ሰዎች ስለ ዛሬው ብቻ ሳይኾን ስለመጭው ሰላምም ሳይቀር መጨነቅ እንደሚገባቸው ነው የገለጹት።

ሰዎች በሌላው ዓለም መኖር በተቸገሩ ሰዓት ወደ ሰላሟ ወደ ሀበሻ ምድር ሂዱ ተብሎ ቃል በተግባር የተከወነባት ሀገረ ኢትዮጵያ ስለምን የሰላም ምድርነቷ ይቅር ሲሉም ይጠይቃሉ።

ሀበሻ የዕውነት አፈር ያለባት ምድር፤ የፍትሐዊ መሪ መገኛ ተብላ የምትታወቅ ሀገር እንደነበረች በአስተምሯችን ተጽፎ ይገኛል ነው ያሉት። ያ ዕውነት ስለምንስ ይጥፋ? ነው የሚሉት። ኢትዮጵያ በዚያ ዘመን ሰው ስለ ሰላም ዋጋ በቅጡ ሳይረዳ ሰላምን እንሰብክ የነበርን ነን፤ እኛነታችን መዘንጋት የለብንም ብለዋል። የእስልምና መነሻ የምትባለው ሳዑዲ ሳትመረጥ የሰላም ምድር ተብላ የተመረጠችው ሀገር ኢትዮጵያ እንደነበረች አስረድተዋል።

ዒድ ማለት የደስታ ቀን ማለት ነው የሚሉት ሼህ አህመድ ደስታን ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ ሰላም ሲኖር ነውና ዒድ ዓል ፈጥር በሰላም እንዲከበር ሁሉም አበርክቶውን ያኑር ብለዋል። በቁርዓን ላይ ተደጋግሞ ተጽፎ የሚገኘውን የትናንቱን የሰላም እሴት እንመልስ ነው የሚሉት።

“የትም ዓለም ላይ ብንሄድ የማናፍርበት ታሪክ መልካሙ የሰላም እሴታችን እንደነበር በመጻሕፍት ተከትቧል” ብለዋል። የት ናችሁ ሲባል ሀበሻ የሚለው ምላሽ ያኮራ እንደነበር ገልጸዋል።

“የነቢላል ሀገር ሀበሻ የሰላም ምሳሌ እንደነበረች ዓለም ያውቃል” ነው ያሉት። ከነበረን ታሪክ አንጻር አሁን ያለው የሰላም እጦት ጥቁር ታሪክ ነው፤ መጻፍ እና ወደ ትውልድ መሻገር የሌለበት ነው ብለዋል።

የእዝነትን እና የመተሳሰብን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በመከተል የሌላቸውን ሁሉ አስበን ዒድ ዓል ፈጥርን እናክብር ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የማፈጥርበት” የምትል የተማጽኖ ድምጽ የወለደችው በጎነት።
Next article“ከታመኑት የታመነች፤ የእውነት ምድር የተባለች”