
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2018ዓ.ም (አሚኮ) ዒድ አል ፈጥር ከታላቁ የረመዳን ጾም ወር በኋላ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በድምቀት የሚያከብሩት ታላቅ መንፈሳዊ በዓል ነው። በዚህ በዓል ደግሞ የሴቶች ሚና ከፍ ያለ ነው።
በረመዳን ጾም መጀመሪያ ቀናት የሚጀምረው የሴቶች ሚና ያለምንም ድካም በፍቅር ደምቆ ቀጥሎ የዒድ አል ፈጥር በዓል በሚከበርበት ቀን ነግሶ ይውላል።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ መሬም አሕመድ ደግሞ በረመዳን ወር እና በኢድ አል ፈጥር ሃይማኖታዊ በዓል ሚናቸውን ከሚወጡ እናቶች አንዷ ናቸው። በቤት ውስጥ ያላቸውን ሚና ከመወጣት ባሻገር በተለያዩ በጎ አድራጎት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይም ይሳተፋሉ።
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከመከሰቱ በፊት በርካታ ሴቶች በቤታቸው እንደሚያደርጉት ሁሉ ከረመዳን ጾም መግቢያ ቀን ጀምሮ የጾም ምግቦችን ለቤተሰባቸው በማዘጋጀት ነበር የሚያሳልፋት።
የኮሮና ቫይረስ የተከሰተበት ጊዜ ግን ከአብሮነት ይልቅ ግላዊነት ግድ የኾነበት ወቅት ነበር። ከእነዛ ቀኖች መካከል ፈጣሪያቸውን ተማምነው በረመዳን ጾም ቁራን ለመቅራት ከቅርብ ጓደኛቸው ጋር ባሕር ዳር መሀል ከተማ ወደሚገኘው ሰላምበር መስጂድ ሲያቀኑ የሰሟት ተማጽኖ ካላቸው ውስጣዊ በጎነት ጋር ተደምራ የዕለት ጉርስ ላጡት እንዲደርሱ ምክንያት ኾነች።
በመስጂድ ውስጥ በኢኮኖሚ ዝቅ ያሉ ሌላ እናት “እህቴ እርቦኝ ነው እባክሽን ለአንድ ዳቦ መግዣ? የማፈጥርበት?” የምትል የተማጽኖ ድምጽ። ያች ድምጽ ከደረቅ ዳቦ ምኞት በበጎ አሳቢ ልቦች በሥጋ ተለውጣ እኒያ ኑሮ ያጎሳቆላቸው እናት እና ሌሎች ጥቂት ሰዎች ዕለቷን በስጋ እንዲያፈጥሩ ምክንያት ኾነች። ለዚህም ወይዘሮ መሬም እና አብረዋቸው የነበሩት ጓደኛቸው ከኪሳቸው አውጥተው ነበር ካላቸው ለሌላቸው ያካፈሉት።
ቀኑን ሲያስታውሱም “ያቺ እናት እራበኝ ያለችኝ ቃል ዛሬም አትረሳኝም” ብለው እንባ ተናነቃቸው። መስጊድ ገብተውም የሴትዮዋ ድምጽ እየታወሰ ቁራን ለመቅራት እንደተቸገሩ ቀኗን በትካዜ አስታወሷት። ወቅቱ ከሚባለው በላይ ከባድ ነበር፤ ቤት ያለው በየቤቱ ተሰብስቦ፤ ያለው ሳይጨነቅ ሲያፈጥር ቤት እና ንብረት የሌላቸውን ብቻ ውጭ ላይ አስቀርቶ ነበር ነው ያሉት።
ያቺ አጋጣሚ ዛሬ ላይ ከእርሳቸው አልፎ ሌሎች በርካታ በጎ ልቦችን አሰባስባ ቁጥራቸው በመቶዎች ለሚደርሱ በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅ ላሉ ሰዎች በረመዳን ጾም ሙሉ ቀኖችን ለማፍጠር እና በኢዳል ፈጥር በዓል በደስታ ለማክበር ምክንያት ኾነች። ሰው ማለት ትርጉሙ ይህ አይደለም? ኢትዮጵያ ማለትስ ይቺ አይደለችም?
ወይዘሮ መሬም ለስምንት ዓመታት ለረመዳን ጾም አፍጥር የሚኾኑ ምግቦችን እና ለስላሳ መጠጦችን ለቤታቸው በማዘጋጀት ከሰዓት ደግሞ በመስጂድ ተገኝተው በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅ ላሉ ሰዎች ማፍጠሪያ እያዘጋጁ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ባለትዳር እና የልጆች እናት ናቸው። ነገር ግን አብሹ፣ ብርዙ፣ ኪኒቶው፣ ዳቦ ቆሎው፣ ገንፎው እና የመሳሰለው ለኢዳ አል ፈጥር አይቀርም።
በንግግራቸው መንፈሳዊ እርካታ እና ደስታ እንጂ ድካም ቦታ የለውም። ለዚህ በጎ ተግባር ፈጣሪያቸው ስለመረጣቸውም በንግግሮቻችን መካከል ደጋግመው ያመሰግናሉ።
ሌሎች ሰዎችም ፈጣሪያቸውን ለማመስገን ምክንያት የኾኑት ወይዘሮ መሬም ለዘንድሮው የዒድ አል ፈጥር በዓልም ቀደም ብለው ነው ዝግጅታቸውን የጀመሩ። ከቀኑ ገፍተው ሌሊቱን አጋምሰው ለበዓሉ የሚኾኑ ምግቦች እንዳዘጋጁም ነግረውኛል።
ሀሳባቸውን ሲያጋሩኝም በበዓሉ ዋዜማ ቤታቸውን ለበዓሉ እያደመቁ እንደኾነ ጠቅሰውልኛል። ታዲያ እንደ ድር እና ማግ የተገመደውን ነባሩን የመተሳሰብ፣ በዓልን በፍቅር እና በአንድነት ከክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ጎረቤቶቻቸው ጋር ለማሳለፍ ለእነሱ የሚኾን ምግብ ማዘጋጀታቸውንም በሀሳባችን መካከል አድምጫለሁ።
በቀሪው ጊዜ ደግሞ በኢኮኖሚያቸው ዝቅ ላሉ ወገኖች መስጂድ ላይ ለሚኖረው የኢድ አል ፈጥር በዓል የምግብ ዝግጅት ሽርጉድ ለማለት እንዳሰቡ ሀሳባቸውን ገልጸውልኛል።
በጎ ልቦች እንዲበዙ ተመኘሁ። ሰላም!
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
