“የጽናት ተምሳሌቱ ቢላል አል ሐበሺ”

11

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በአደባባይ የሚከወኑ ሁለት ትላልቅ በዓላት አሉ። አንደኛው የዒድ አልፈጥር በዓል ነው።

ዒድ ማለት ተደጋጋሚ የሚመጣ፤ በየዓመቱ የሚተካካ የሚል ትርጉም አለው። በዓሉ የረመዳን ወር መጠናቀቅን ተከትሎ የሚመጣ የደስታ እና የምሥጋና በዓል እንደኾነም የሃይማኖቱ አባቶች ያብራራሉ።

በዚህ ወር ታዲያ አንድ ስም ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ይነሳል፤ እሱም ቢላል አል ሐበሺ ነው።

ሐበሻው ቢላል በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አለው። ስመ ጥር እና ዝነኛም ነው። ከታሪክ ባለፈም ጥልቅ መንፈሳዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ትርጉም ይሰጠዋል።

ለሃይማኖቱ ሲል የደረሰበትን ግፍ እና መከራ በጽናት በመቋቋሙ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የጥንካሬ ምንጭ በመኾን ይጠቀሳል። እርሱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳን ለማንነት እና ለሃይማኖቱ መታመንን ለዓለም አሳይቷል። የቁጥብነት፣ የጽናት እና የጀግንነት ተምሳሌት ተደርጎም ይነሳል።

ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያዊያን የሃይማኖቱ ተከታዮች “በአምላክ ዘንድ የተሻለው፣ ቀናው እና አላህን ፈሪው ነው” የሚለውን መርሕ በተግባር ከሚገልጥላቸው ውስጥ ህያው ምስክር መኾንም ችሏል።

ቢላል አል ሐበሺ ኢትዮጵያን በወቅቱ በነበረው የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ማኅበረሰብ ዘንድ በማስተዋወቅም ባለውለታ ተደርጎ ይነሳል። “የሐበሻው ቢላል” የሚለው ስያሜ በራሱ ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ብሔራዊ ኩራት እና በዓለም አቀፉ የሙስሊም ማኅበረሰብ ዘንድ ያላቸውን ክብር የሚያጎላ አጋጣሚም ፈጥሯል።

የአማራ ክልል እስልምና ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ኢብራሂም ከአሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በእስልምና ነብይ ኾነው በመካ ላይ በሚወጡበት ሰዓት ቢላል አል ሐበሺ እስልምናን ከተቀበሉ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መካከል መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

ሐበሻው ቢላል አዛን አድራጊ ኾኖ በነብዩ ሙሐመድ የተመረጠውም በዕውቀቱ፣ በታማኝነቱ እና በጽናቱ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያን በወቅቱ ለነበረው ሙስሊሙ ማኅበረሰብ አስተዋውቋል። የታማኞች እና የአዋቂዎች ሀገር መኾኗንም አሳይቷል ነው ያሉት።

እንደ ሼህ መሐመድ ኢብራሂም ገለጻ በእስልምና በቀለም፣ በሃብት እና በሥልጣን ሰዎችን ማበላለጥ ተቀባይነት የለውም። በእስላም ሁሉም ሰው እኩል ነው። ቢላል አል ሐበሺም እስልምናን ሲቀላቀል እንደማንኛውም ሰው እኩል መብት ነበረው ብለዋል። የእኩልነት እና የነጻነት ተምሳሌት እንደኾነም ነው የጠቀሱት።

የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ከቢላል ብዙ መማር ይቻላል ብለዋል። ከዘር፣ ከቀለም እና ከሥልጣን ይልቅ ጽናት፣ መታመን እና ዕውቀት መለኪያ መኾን ይገባቸዋል ብለዋል። ሰውን በማንነቱ ማግለል አይገባም። ሰው ሁሉ እኩል መኾኑን መቀበል ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በወቅቱ በመካ መዲና እስልምናን የተቀበሉ ብቻ ሳይኾኑ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የሥራ ባልደረባ የነበሩ ብዙ ሐበሾች እንደነበሩም አንስተዋል። በየትኛውም ቦታ የነበሩ ሐበሾች የተከበሩ እና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው እንደነበሩ ነው የተናገሩት።

ቢላል ለኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በታሪክ የሚነበብ ሰው ብቻ አይደለም፣ የመንፈስ ወንድም፣ የጽናት ተምሳሌት፣ የነጻነት መምህር እና የማንነት መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወገኖቻችን እንደኛው ደስ ብሏቸው እንዲውሉ ማድረግ ይገባል”
Next article“የማፈጥርበት” የምትል የተማጽኖ ድምጽ የወለደችው በጎነት።