“ወገኖቻችን እንደኛው ደስ ብሏቸው እንዲውሉ ማድረግ ይገባል”

7

ባሕርዳር፡ መጋቢት 11/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለ1ሺህ 447ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ የኾነውን መረዳዳት ታሳቢ ያደረገ ሊኾን እንደሚገባ የሃይማኖቱ አባቶች ተናግረዋል፡፡

በእስልምና አስተምህሮ ውስጥ መረዳዳት የአንድ ሙስሊም የሃይማኖቱ መገለጫ እና የማኅበራዊ ሕይወት መሠረት እንደኾነ ይታመናል፡፡ አስተምህሮቱ አንዱ ሲታመም ሌላው የሚሰማው ጥልቅ ትስስር እንዲኖር የሚያስተምር በመኾኑ ይህንኑ በጎ ተግባር በተግባር ለመግለጥ ከሁሉም የሃይማኖቱ ተከታዮች ይጠበቃል፡፡

እንደ ሃይማኖቱ አባቶች መረዳዳት በእስልምና ሥርዓት ውስጥ በሁለት መንገድ ይገለጻል፡፡ የመጀመሪያው ሀብታሞች ካላቸው ንብረት ላይ ለድሆች የሚሰጡት እና እንደ ግዴታ የሚቆጠረው የዘካ ሥርዓት ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በማንኛውም ጊዜ እና ሁኔታ ዕውቀትን፣ ጉልበትን እና ገንዘብን ጨምሮ በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚደረግ የሰደቃ ተግባር ነው፡፡
ለዚህም ነው የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ኡስታዝ አህመድ ካሳ ሙዘይን ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ውስጥ የኾኑ ወገኖችን ማዕድ በማጋራት ሊኾን ይገባል ነው ያሉት፡፡

እያንዳንዱ ግለሰብ በነፍስ ወከፍ ሁለት ኪሎ ተኩል እህል በማውጣት ለምስኪኖች መስጠት እስላማዊ ግዴታ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ወገኖቻችን እንደኛው ደስ ብሏቸው እንዲውሉ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አማካሪ እና የባሕር ዳር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የትምህርት ዘርፍ ኀላፊ ሼህ ጀውሐር ሙሀመድ የረመዳን ወር የትዕግስት እና ራስን የመፈተሻ ወር ነው ብለዋል፡፡ በወሩ የተገኘው መንፈሳዊ ጥንካሬ እና የመረዳዳት ባሕል በበዓል ወቅትም ኾነ ከበዓል በኋላ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

እንደ ሼህ ጀውሐር ሙሀመድ መረዳዳት እና መተሳሰብ የእስልምና መሠረታዊ እሴቶች ናቸው፡፡ የዒድ አል ፈጥር ደስታ ለሁሉም እንዲዳረስ ማድረግ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነውም ብለዋል፡፡

ይህም ለሀገራዊ ሰላምና አብሮነት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው የገለጹት፡፡
በዓሉን ስናከብር ከሁሉም ማኅበረሰብ እና ከሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች ጋር በመተሳሰብ ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡

የቆዩ የደግነት እሴቶችን ማስቀጠል ይገባል ያሉት ሼህ ጀውሐር መረዳዳት የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር የጀነት መግቢያ በር መኾኑንም አሳስበዋል። በተጨማሪም በረመዳን ወር ላይ የሚደረጉ መልካም ተግባራት ከአሏህ ዘንድ በእጥፍ ምንዳ እንደሚያሰጡ ገልጸዋል፡፡

አንድ ሰው አንድን ሰው ካስፈጠረ ጾሞ የነበረውን ሰው ያህል ምንዳ ከአሏህ ዘንድ ያገኛልም ብለዋል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙም በረመዳን ወር ያሳየውን የመረዳዳት፣ የሰላምና የደግነት እሴቶች ከበዓል በኋላም አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡

ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleረመዳን የዕዝነት እና የመዳን ወር ነው።
Next article“የጽናት ተምሳሌቱ ቢላል አል ሐበሺ”