
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የረመዳን ጾም በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ወር ተብሎ ይጠራል። በዚህ ወር ቅዱስ ቁርዓን ለሰው ልጆች ሁሉ ይደርስ ዘንድ ለነብዩ ሙሐመድ መውረድ የጀመረበት ወር በመኾኑ ምንዳው ከሺህ ወር በላይ እንደኾነ የእስልምና አስተምህሮ ያስረዳናል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሐመድ ኢብራሒም የረመዳን ጾም ለመጀመሪያ ጊዜ መጾም የተጀመረው እንደ ሂጅራ አቆጣጠር በሁለተኛው ዓመተ ሂጅራ ወይም እ.አ.አ በ624 ነው ብለዋል።
በዚህ ወር ለጾም ዕድሜው የደረሰ እና ጤነኛ ለኾነ ሙስሊም ሁሉ ግዴታ ነው ይላሉ። የጾመ በረከት ወይም ምንዳ ያገኛል፤ ያልጾመ በፈጣሪው ዘንድ እንደሚያስጠይቅም አስተምህሮው ያስረዳል ነው ያሉት።
የቅዱስ ቁርዓን ወር ተብሎ እንደሚጠራ የተናገሩት ሼህ ሙሐመድ በቁርዓን በርካታ መለኮታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊ እና ሕጋዊ የጸሎት ትምህርቶች እንዲታወሱ እና እንዲሠርጹ የሚደረግበት ነውም ብለዋል።
የረመዳን ወር ጾም ከሌሎች የሚለዩባቸው ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥም፦
👉 ወሩን ሙሉ መጾም ከእስልምና ማዕዘናት አንዱ ነው፤
👉 ቁርዓን በብዛት የወረዱበት በመኾኑ፤
👉 ከ1 ሺህ ወራት በላይ የኾነችው ሌሊት የምትገኝበት በመኾኗ፤
👉መረዳዳት፣ ቸርነት እና ስጦታ የነገሰበት በመኾኑ፤
👉 አምኖ እና ምንዳውን ከአላህ ፈልጎ የረመዳንን ወር የጾመ ሰው ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል፤ የመልካም ሥራዎች የሚበዙበት እና እጥፍ ድርብ የሚኾንበት በመኾኑ፤
👉 የሌሊት ሶላት በአንድነት የሚደረግበት በመኾኑ፤
👉 በረመዳን ወር የጀነት በሮች የሚከፈቱበት፤ የጀሀነም በሮች የሚዘጉበት እና ሰይጣናት የሚታሰሩበት ወር መኾኑ ተጠቃሾች እንደኾኑ ጠቅሰዋል።
ረመዳን የመረዳዳት፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የወንድማማችነት እና የአንድነት መገለጫ ወር መኾኑንም ነው የገለጹት።
በዚህ ወር ብዙ ስጦታዎች እና ልግስናዎች ከአላህ ዘንድ ወደ ባሮቹ የወረዱበት ነውም ብለዋል። የእምነቱ ተከታዮችም አላህን እያሰቡ አስተምህሮውን፣ ሕግጋትን እና ትዕዛዛት ተግባራዊ ያደርጋሉ፤ ይጸልያሉም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
