
ባሕርዳር፡ መጋቢት 10/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለ1ሺህ 447ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል። ጉባዔው መጋቢት 10/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በዓሉ የጾም መፍቻ ብቻ ሳይኾን የምሥጋና፣ የመንፈሳዊ ተሃድሶ እና የማኅበራዊ ትስስር መገለጫ መኾኑን ገልጿል።
በተቀደሰው የረመዳን ወር የታዩት የጾም፣ የጸሎት፣ የምጽዋት (ዘካት) እና ራስን የመግዛት ተግባራት ሰውን ወደ ፈጣሪ የሚያቀርቡ እና ማኅበራዊ ሕይወትን የሚያጠናክሩ ታላቅ እሴቶች መኾናቸውን ጉባዔው አመልክቷል።
እነዚህ የርህራሄ፣ የትሕትና እና የይቅርታ እሴቶች ሁሉም የሃይማኖቱ ተከታይ ማኅበረሰቦች የሚጋሯቸው የሰውነት መገለጫዎች በመኾናቸው በፍቅር፣ በአንድነት እና በሰላም አብሮ ለመኖር መሠረት እንደሚኾኑም ተገልጿል።
ኢትዮጵያውያን ለረጅም ዘመናት በሃይማኖት ሳይለያዩ በመከባበር እና በሰላማዊ አብሮነት መኖራቸውን ያስታወሰው መግለጫው አሁንም ኢትዮጵያ እርቅ፣ አንድነት እና ዘላቂ ሰላም እጅጉን በሚያስፈልጋት ወቅት ላይ እንደምትገኝ ጠቁሟል።
በመኾኑም ሁሉም ዜጎች እና የሃይማኖቱ ተከታዮች የመቻቻል እና የሰላም እሴቶችን እንዲያጠናክሩ ጉባዔው ጥሪ አቅርቧል።
በተለይም የሃይማኖት መሪዎች እና ተቋማት በማኅበረሰቡ ውስጥ የሰላም እና የአብሮነት መልዕክትን በማስፋት ለማኅበራዊ መረጋጋት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም አሳስቧል።
ጉባዔው በመጨረሻም የዒድ አል-ፈጥር በዓል ለሃይማኖቱ ተከታዮች ደስታን፣ ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ደግሞ ዘላቂ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ተስፋን እንዲያመጣ መልካም ምኞቱን ገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
