የሳይበር ወንጀል ተጠያቂነት ምን ድረስ ነው?

5
ባሕር ዳር:መጋቢት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በቴክኖሎጂ በረቀቀው በዚህ ዘመን የሳይበር ደኅንነት የሀገር ሉዓላዊነት እና የግለሰቦች ደኅንነት መገለጫ ኾኗል። ኢትዮጵያም የዲጂታሉን ዓለም ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጠንካራ የሕግ መሠረቶችን ጥላለች።
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ የመረጃ ማዕከል ባለሙያ የኾኑት ብዙአየሁ በፍቃዱ ሀገሪቱ የሳይበር ወንጀልን ለመግታት እና የዜጎችን መረጃ ለመጠበቅ ሰፊ የሕግ እና የተቋም ዝግጅት አድርጋለች።
✍️ሕጎች ምን ይላሉ?
​ኢትዮጵያ የሳይበር ወንጀልን ለመከላከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀመው የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 ነው። ይህ አዋጅ በዲጂታል ዓለም የሚፈጸሙ እንደ ሀኪንግ (ያለፈቃድ መግባት)፣ የመረጃ ጠለፋ፣ የማጭበርበር ድርጊቶች እና የሕፃናት “ፖርኖግራፊ” የመሳሰሉ አስጸያፊ ድርጊቶችን በወንጀል በመፈረጅ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል።
​ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ የጸደቀው እና ተስፋ የተጣለበት የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 1321/2016 የዜጎችን የግል መረጃ አያያዝ ላይ ትኩረት ያደርጋል።
ማንኛውም መረጃ የሚሠበሥብ ተቋም የሠበሠበውን መረጃ ለተፈለገው ዓላማ ብቻ የመጠቀምና ደኅንነቱን የመጠበቅ የሞራል እና የሕግ ግዴታ እንዳለበት ያስገነዝባል።
እንዲኹም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሱ የጥላቻ ንግግሮችን እና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመግታት የወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 የዲጂታል ሰላምን ለመጠበቅ ጉልህ ድርሻ አለው።
ከዚህም ባለፈ የወንጀል ሕግ፣ የቴሌኮም መጭበርበር ወንጀል አዋጅ እና ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ስለ ሳይበር ደኅንነት ድንጋጌዎችን አሥቀምጠዋል።
ባለሙያዋ እንዳሉት ​ሕጎቹን መሬት ለማውረድ እና የሀገሪቱን የሳይበር ድንበር ለመጠበቅ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር (ኢመደአ) እየሠራ ይገኛል። ተቋሙ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ ከመከላከል ባለፈ ወንጀል ሲፈጸምም የቴክኒክ ምርመራዎችን በማካሄድ ለሕግ አስከባሪዎች የጀርባ አጥንት ኾኖ ያገለግላል።
አሥተዳደሩ በ2018 የመጀመሪያው ስድስት ወር ከ27 ሺህ በላይ የሚኾኑ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፍ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።
ወንጀል ፈጽሞ በተገኘ አካል የገንዘብ መቀጮን ጨምሮ ከቀላል እስራት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣም ገልጸዋል።
በሀገር መሠረተ ልማት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጡም ነው የገለጹት።
ይኹን እንጅ የሳይበር ወንጀል ድንበር የለሽ መኾኑ የአጥቂዎችን አድራሻ ለመለየት ፈታኝ እንደኾነ አንስተዋል። በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የግንዛቤ ማነስ አሁንም ትልቅ ተግዳሮት መኾኑንም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። የርእሰ መሥተዳድሩ ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
Next article“የዒድ አል-ፈጥር ዕሴቶች ለዘላቂ ሰላም እና እርቅ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያላቸው በመኾኑ ሊጠናከሩ ይገባል” የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ