
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በቅርብ ሳይኾን በሩቁ ወጥኖ መሥራት ሀገርን ያሳድጋል፤ ለግለሰቦችም ለውጥ የራሱ ሚና አለው።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ እንደ ሀገር የተጀመሩ ኢንሼቲቮች ምን ያክል ለውጥ እያመጡ እንደኾነ ጠይቋል።
እንደ ሀገር ከተጀመሩ ኢኒሼቲቮች መካከል የኢትዮ ኮደርስ አንደኛው ነው። ይህ ኢኒሼቲቭ የወጣቶችን ሕይወት እየቀየረ ነው። ቴክኖሎጂን መሠረት በማድረግ ወጣቶች በመላው ዓለም ተወዳዳሪ እና የሥራ እድል ተጠቃሚ እያደረ ነው።
በዚህ ኢኒሼቲቭ ተጠቃሚ ከኾኑት ወጣቶች መካከል በኃይሉ ደምሌ አንደኛ ነው። ኮምፒውተር ኢንጅነሪንግ ተምሮ ለብዙ ጊዜ ሥራ አጥቶ መቆየቱን ተናግሯል።
ከጊዜ በኋላ ግን በኢትዮ ኮደርስ ተጠቃሚ እንደኾነ ገልጿል። አሁን ላይ በተመረቀበት ሙያ እየሠራ ነው። በኦንላይን የሚደረጉ ሥራዎች ለእርሱ ሕይወቱን እየቀየሩለት መኾናቸውን ተናግሯል።
በሀገሩ ኾኖ የአውሮፓ ሀገራትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ካሉ የቴክኖሎጂ ሰዎች ጋር በጥምረት የሶፍትዌር ልማት ፕሮጄክቶች ላይ እየተሳተፈ ጥሩ ገቢ እንደሚያገኝም ገልጿል።
በሀገር ውሰጥም ከትልልቅ ኢንዱስትሪዎች እስከ አስጎብኝ ድርጅቶች ድረስ በፈጠረው ጥምረት ቴክኖሎጂው እንደጠቀመው አስረድቷል።
ሌሎች ወጣቶችም ዘርፉ ከሚታሰበው በላይ ጥቅም ያለው መኾኑን ተረድተው እንዲጠቀሙበት መክሯል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ሞክትል ኀላፊ አማረ ዓለሙ እንደ ሀገር በተጀመረው የ5 ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ወጣቶችን እያሰለጠኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት 198 ሺህ 792 ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ወስደዋል። ዘንድሮ ደግሞ በስድስት ወራት ውስጥ 192 ሺህ 198 ወጣቶች ሠልጥነዋል ነው ያሉት።
ከሀገራዊ ኢንሼቲዎች ባሻገር በክልላዊ ኢኒሼቲቮች ወጣቶች ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል። በዲጂታል አማራ ኢኒሼቲቭ 20 ሺህ ወጣቶች እየተሳተፉ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የዲጂታል አማራ ኢኒሼቲቨ በርካታ ውጤቶች እየተገኙበት ያለ ሥራ እንደኾነ የጠቆሙት ምክትል ኀላፊው ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለማቀፍ ድረስ ተወዳዳሪ የኾኑ ለሀገራቸውም ኾነ ለራሳቸውም መጠቀም የቻሉ ወጣቶችን መፍጠር እየቻለ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
