የሕግ ባለሙያዎች የወጡ ሕጎችን መከታተል እና ማሥፈጸም አለባቸው።

5
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በፍትሐብሔር የፍትሕ አሥተዳደር ዘርፍ ሕጎች ላይ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ገምግሟል።
በግንባታ ውል አሥተዳደር፤ በግዥ ውል አሥተዳደር እና አጠቃላይ የሕግ አወጣጥ ላይ የወጡ ሕጎች እና ደንቦች ዙሪያ ነው ውይይት የተደረገው።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ወንዳቸው ሠራው ከዚህ በፊት የነበሩ ሕጎች ረጅም ጊዜ በሥራ ላይ የቆዩ እና በየጊዜው ምላሽ የሚሹ ኾነው በመገኘታቸው የዳሰሳ ጥናት አስፈልጓል ብለዋል። የተቋማት የሕግ ባለሙያዎች የወጡ ሕጎችን መከታተል እና ማሥፈጸም አለባቸው ነው ያሉት።
አዲስ የግዥ አዋጅ መውጣቱንም ተናግረዋል። በቴክኖሎጂ የታገዘ፤ ፍትሐዊ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት እና ከአድሎ የፀዳ የግዥ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ይህም የክልሉን የሕግ የበላይነት እንዲረጋጥ ያደርጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የፍትሐብሔር የፍትሕ አሥተዳደር ዳይሬክተር መንበሩ ማናዬ የዳሰሳ ጥናቱ በፍትሐብሔር የፍትሕ አሥተዳደር በግንባታ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ሊፈታ የሚያስችል ነው ብለዋል። የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብትን በአግባቡ ለማሥተዳደር እንደሚያግዝም ገልጸዋል። የወጡ ሕጎች ተግባራዊ እንዲኾኑ ባለ ድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የሕግ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አስመላሽ በተሻሻለው የሕግ አዋጅ የተገኘውን የዳሠሣ ጥናት መሠረት በማድረግ በቀጣይ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበሰሜን ወሎ ዞን 502 የልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው።
Next articleበቴክኖሎጂ ላይ እየተሰጡ ያሉ ሥልጠናዎች የወጣቶችን ሕይወት እየቀየሩ ነው።