ኢትዮጵያ የሰላም ካባ መልበስ አለባት።

13
ባሕርዳር፡ መጋቢት 10/2018ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም በግል ሕይወት፣ በማኅበረሰብ እና በሀገር ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ያለው ነው። ኾኖም ግን ባለፋት ጥቂት ዓመታት ይህ ከፍተኛ ስፍራ ያለው ሰላም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ችግሮች ገጥመውታል።
አሚኮ ዲጅታል ሚዲያም እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም እንዲኖር እና እንዲጸና የፖለቲካ ፓርቲዎች እያደረጓቸው ያሉ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር በሁሉም አካባቢ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከአቻ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመኾን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ለሀገር በሚበጁ የሰላም ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደርጉ እንደነበርም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከዳር እስከዳር ብሔራዊ አንድነቷ ተጠብቆ በሰላም መኖር የሚቻልባት ሀገር እንድትኾን ፓርቲው እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ይህንንም እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት ፓርቲ (ኢዴኅፓ) ሊቀመንበር ገብሩ በርሄ የሀገር ሰላም እንዲጸና ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች አሁንም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።
በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታትም እየተካሄዱ ያሉ ግልጽ ውይይቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ይህንንም ሀሳብ ፓርቲው በተለያዩ ውይይቶች ላይ ሲያቀርብ እንደነበር እና አሁንም እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሰላም ከሌለ ፓርቲዎች በሁሉም አካባቢዎች ሊንቀሳቀሱ አይችሉም ያሉት ሊቀመንበሩ ሀገሪቱ በአጠቃላይ የሰላም ካባ መልበስ አለባት ብለዋል። ለዚህም ሁላችንም የሰላም አምባሳደሮች መኾን አለብን ነው ያሉት። በቀጣይም ዘላቂ ሰላም እስኪመጣ እንደ ፓርቲ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የአማራ ክልል አስተባባሪ መሠረት ተሠራ እንደ ፓርቲ ሀገራዊ እና ክልላዊ ሰላም እንዲጸና፣ የፖለቲካ ምህዳሮች እንዲሰፉ፣ ጦርነት እንዲቆም እና በመንግሥት በኩል እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
ሀገር ሰላም እንድትኾን እና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሚሠራ ሥራ ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ እንዳልኾነም አንስተዋል። እንደ ኢሕአፓም የራሳችን ሚና መወጣት አለብን የሚል እሳቤ ይዘን ጥረቶች እያደረግን ነው ብለዋል።
ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ጊዜ እና በድህረ ምርጫ ሰላማዊ ኹኔታዎች እንዲኖሩም እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። ሀገር እና ሕዝብ ሰላም እንዲኾን ፓርቲው ከመንግሥት ጋር እየሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ለኢድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። መልእክታቸውም እንደሚከተለው ቀርቧል፦
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን 502 የልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው።