
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለ1ሺህ 447ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ኡስታዝ አህመድ ካሳ እንኳን ለዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የረመዳን ወርን በጾም፣ በዱዓ፣ በሰደቃ እና በመረዳዳት ማሳለፉን ገልጸዋል።
ረመዳን የነፍስ ሰላም የሚረጋገጥበት እና የውስጥ ሰላም የሚገነባበት ታላቅ ወር መኾኑንም አብራርተዋል። ይህ ወር ለሙስሊሞች ብቻ ሳይኾን ለኢትዮጵያውያንም በጋራ የሚናፈቅ እና አብሮነት የሚጠናከርበት የቸርነት ጊዜ በመኾኑ በወሩ ሲከናወኑ የነበሩ መልካም ተግባራት ከረመዳን በኋላም ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሙስሊሙ ማኅበረሰብ በዓሉን ሲያከብር አንድነትን እና ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊኾን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በተለይም በሰላም እጦት እና በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ፣ ችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች፣ ለምስኪኖች በማዘን እና ማዕድን በማጋራት ደስታውን የጋራ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዘካተል ፊጥር ለምስኪኖች መስጠት እስላማዊ ግዴታ መኾኑን የገለጹት ኡስታዝ አህመድ ወገኖቻችን ደስ ብሏቸው እንዲውሉ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ለሀገር እና ለክልል ሰላም ዱዓ ማድረግ ብሎም በሁለንተናዊ ልማት ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል። መልካም ነገር የሚጀምረው ከቤተሰብ በመኾኑ እያንዳንዱ ሙስሊም ለሰላም እና ለልማት የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዓሉ በዒድ ሶላት ቦታዎች ላይ በጋራ እና እስላማዊ ሥነ ምግባርን በተላበሰ ሁኔታ እንደሚከበር ተናግረዋል።
በዓሉ ስለ ሰላም፣ አንድነት እና መከባበር የሚጸናበት፤ ከሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች ጋር የመተሳሰብ እና የቆዩ ደግ እሴቶች የሚጠናከሩበት ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
