
ባሕር ዳር:መጋቢት 10/2018 ዓ.ም
በቴክኖሎጂ ዘመን የሰዎች ዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ከዲጂታል ምኅዳሩ ጋር በጥብቅ መቆራኘቱን ተከትሎ የሳይበር ጥቃት ሥጋቶች ከምንጊዜውም በላይ እየጨመሩ እንደሚገኙ የአሜሪካው የሳይበር እና የመሠረተ ልማት ደህንነት ኤጀንሲ (CISA) መረጃ ያሳያል።
እንደ ኤጀንሲው መረጃ የሳይበር ጥቃት በዲጂታል መንገድ መረጃን ለመስረቅ፣ ለማጥፋት ወይም አገልግሎት ለማቋረጥ የሚሰነዘር አደገኛ ሙከራ ነው።
የሳይበር ደህንነት (Cyber security) መረጃዎችን፣ የመረጃ መረቦችን፣ ኮምፒውተሮችን እና የአሠራር ሂደቶችን ከጥቃት ወይም ከሥርቆት የመጠበቅ ሂደት ነው። ይህ ዘርፍ ሚስጥራዊ መረጃዎች ባልተፈቀደላቸው አካላት እጅ እንዳይገቡ መከላከልን እና ዲጂታል ሥራዎች ያለመስተጓጎል እንዲከናወኑ ማስቻልን ዋና ዓላማው ያደርጋል።
ዘርፉ የቴክኖሎጂ ውጤት ብቻ ሳይኾን የግለሰቦች ንቃተ ሕሊና እና የተቋማት ጠንካራ መመሪያዎች ተቀናጅተው የሚፈጥሩት “የደህንነት ጋሻ” እንደኾነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
እንደ ኤጀንሲው መረጃ የሳይበር ምህዳርን ደህንነት መጠበቅ በአኹኑ ወቅት እጅግ ፈታኝ እየኾነ መጥቷል።
ጥቃት አድራሾች ከየትኛውም የዓለም ጥግ ኾነው የመንቀሳቀስ አቅም ያላቸው መኾኑ አንዱ ምክንያት ነው።
የሳይበር ምህዳሩ ከዜጎች አካላዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መኾኑ እና በውስብስብ የሳይበር መረቦች ውስጥ ያሉ ተጋላጭነቶችን ለመቀነስ ያለው አስቸጋሪነትም የተጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው።
አስተማማኝ የሳይበር ደህንነት ልምዶችን መተግበር ለግለሰቦችም ኾነ ለድርጅቶች አማራጭ የሌለው ጉዳይ መኾኑ ተመላክቷል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያም የሳይቨር ጥቃት ሙከራ እየጨመረ ይገኛል።
በ2017 ዓ.ም ብቻ 13 ሺህ 496 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ከአሥተዳደሩ የተገኘ መረጃ ያሳያል።
በ2018 የመጀመሪያ ሥድስት ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ላይ 27 ሺህ 773 የሳይበር ጥቃቶች ተሰንዝረዋል።
ከእነዚህ ውስጥም 99 በመቶው እንዲከሽፉ መደረጉ ተገልጿል።
የቴክኖሎጅ ውስብስብነት፣ የእውቀት ውስንነት እና የአሠራር ሥርዓት ክፍተት አጋላጭ ምክንያቶች ኾነው ተቀምጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
