በጎንደር ከተማ በከብት ማድለብ የተሠማሩ ግለሰቦች ውጤታማ መኾናቸውን ተናገሩ።

6
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በከብት ማድለብ ሥራ ተሠማርተው ያገኘናቸው አቶ ፈንታሁን መከተ ለአሚኮ እንደተናገሩት ቀደም ሲል በጌጠኛ ድንጋይ ማምረት ሥራ ተደራጅተው ቆይተዋል። ሥራው ሲቋረጥ ተስፋ ሳይቆርጡ በ50 ሺህ ብር ካፒታል ወደ ከብት ማድለብ ሥራ ገብተዋል።
ተግባሩን በማስፋትም አሁን ላይ ካፒታላቸውን ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችለዋል። ቤተሰባቸውን ከማሥተዳደር አልፈው የከተማ ቦታ እንደገዙ እና በሥራው ውጤታማ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ዲያቆን ሳሙኤል መርሻ እና ወጣት ውዱ አማረ በቤተሰብ ድጋፍ 18 ከብቶችን እያደለቡ ይገኛሉ። በየሦስት ወሩም ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ምህረት መልካሙ የከብት እርባታ ድርጅት በአሁኑ ወቅት ከ30 በላይ በሬዎችን እያደለቡ ይገኛሉ። ለ11 ግለሰቦችም የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን የድርጅቱ ተወካይ አድኖ መልካሙ ለአሚኮ ተናግረዋል። ከመንግሥት የሙያ እና የሕክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው መኾኑን ነው የገለጹት።
ሥራውን አስፋፍቶ የበለጠ ተጠቃሚ ለመኾን የቦታ እና የመኖ እጥረት እንዳለባቸው ወጣቶቹ አንስተዋል። ወጣቶች ሥራ ሳይንቁ በከብት ማድለብ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል።
የጎንደር የከተማ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት መምሪያ የኤክስቴንሽን እና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ ሀብታሙ ዘገየ የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብርን በሁለት አሃዝ እድገት ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የቦታ ችግሩን ለመፍታት 33 ሄክታር መሬት መለየቱንም ጠቁመዋል። የመኖ አቅርቦትን ለማሻሻል ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር ትስስር በመፍጠር አረንጓዴ መኖዎችን፣ የፋብሪካ ውጤቶችን እና የሰብል ተረፈ ምርቶችን በስፋት ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
እንስሳት አርቢዎች በዓመት አራት ጊዜ ምርታቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ ታስቦ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ለዚህም በዘመናዊ መንገድ የክላስተር አሠራርን በመከተል የሙያ እገዛ እየተጠናከረ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየዶክተር አምባቸው መኮንን ፋውንዴሽን ጾታ ተኮር ጥቃትን ለመከላከል እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት አስጀመረ።
Next articleየሳይበር ሥጋት እና የዲጅታል ደህንነት ተግዳሮቶች።