
ባሕርዳር፡መጋቢት 09/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ከላስታ ወረዳ እና ከላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር “ለሰላም ዘብ እንቆማለን የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም እጦት የቱሪዝም እንቅስቃሴን በእጅጉ እንደጎዳው ተናግረዋል። አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ የላሊበላ ከተማ የአስፋልት ንጣፍ ሥራ በፍጥነት እንዲሠራ እና ለነአኩቶላብ ቤተ ክርስቲያን ቅርስ እድሳት እንዲደረግ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
“ሰላም በጸጥታ አካል ብቻ አይመጣም፤ ለሰላም ልንተጋ ያስፈልጋል” ያሉት ነዋሪዎቹ የአካባቢያቸውን ሰላም ለማጽናት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የከተማዋ የመንገድ መሠረተ ልማት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ የላቀ መኾኑንም ተናግረዋል።
በከተማዋ ባለው አንጻራዊ ሰላም የቱሪዝም እንቅስቃሴው እየተነቃቃ መምጣቱን ያነሱት አሥተዳዳሪው የቱሪዝም ፍሰቱ ውጤታማ እንዲኾን ማኅበረሰቡ ሰላምን አስጠብቆ መዝለቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮምሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል ማኅበረሰቡ ውስጣዊ አንድነቱን በማጠናከር ሰላሙን ማጽናት እንዳለበት አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ በአካባቢው የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲስፋፉ እና የቅዱስ ላሊበላ ቅርስ ጥገና እንዲደረግለት ማኅበረሰቡ ሰላሙን ማጽናት እንዳለበት ተናግረዋል።
ተደራጅቶ አካባቢን በመጠበቅ እና ውስጣዊ አንድነትን በማረጋገጥ ሰላም እንዲመጣ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ በመኾን ሕዝባዊ እና ሕጋዊ መንግሥት እንዲመሠረት ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎችን መንግሥት መልሶ ማቋቋሙን አንስተዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ እያደረጉት ላለው ጥረት አመሥግነዋል። አሁንም በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የምርጫ ካርድ በማውጣት እና በመምረጥ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ እንዲኾን ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
