
አዲስ አበባ: መጋቢት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ ከ100 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወገኖች ማዕድ አጋርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የረመዳን ጾም ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የማዕድ ማጋራት እና የኢፍጣር ሥነ ሥርዓት በከተማዋ በስፋት ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል። የዛሬው ድጋፍም ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ያለንን ለመካፈል እና በዓሉን ደስ ብሏቸው እንዲያሳልፉ ያደረግነው ነው ብለዋል።
ድጋፉ የተለያዩ ድርጅቶችን በማሥተባበር የተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የማዕድ ማጋራቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ ከ100 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወገኖች መደረጉንም ተናግረዋል። በዚህ በጎ ተግባር ለተሳተፉ ድርጅቶች እና በጎ ፈቃደኞች ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በከተማው የከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ማዕድ ከማጋራት ባሻገር በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ኅብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማሥተባበሪያ ኮሚሸን ኮሚሽነር ይመር ከበደ የመልካም ሥራ መከወኛ በኾነው የረመዳን ወር የአቅም ውስንነት ላለባቸው ከ27 ሺህ በላይ ሙስሊም ወገኖች ሳይቸግራቸው እንዲያሳልፉ የሚያስችል ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
መጭውን የኢድአልፈጥር በዓልም በማስመልከት አብሮነትን እና መተሳሰብን ለማጎልበት ዛሬ ከ100 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች ማዕድ አጋርተናል ነው ያሉት።
ድጋፉ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለዝቅተኛ ነዋሪዎች እና የመንግሥት ሠራተኞች ጭምር የተደረገ ነው።
ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም ለተደረገላቸው ድጋፍ
አመስግነዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሔም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
