
ባሕርዳር፡መጋቢት08/2018ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ለአንድ ሀገር ብዙ ፋይዳ ያለው የዴሞክራሲ መሠረት ነው። ብዙ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ፍላጎቶች ላሉባቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች ደግሞ ሚናው ጉልህ ነው።
ለዚህም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንደ ሀገር እና እንደ አማራ ክልል በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይወዳደራሉ። ከእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) አንዱ ነው።
የፓርቲው ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር ፓርቲው እንደ ሀገር እና እንደ ክልል በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመወዳደር በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ በሀገሪቱ አብዛኛዎቹ ቦታዎች ለቅድመ ምርጫ ተግባራት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ተናግረዋል።
ፓርቲው በየአካባቢው ያሉ እጩዎች አስቻይ ሁኔታዎችን አጣጥመው በመጠቀም ቅስቀሳዎችን በሰፊው እንዲሠሩ ይደረጋልም ብለዋል።
እስከ አሁን በነበሩ ጊዜያት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ፓርቲው ሲሠራ እንደቆየም አስረድተዋል።
ፓርቲው የድረስ ድረስ የኾነ አካሄድ የለውም፤ ለሁሉም ዝግጁ ኾኖ የሚሠራ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት።
ፓርቲው 1ሺህ 100 እጩዎችን በማቅረብም ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ለማሸነፍ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ሌላኛው እንደ ሀገር እና እንደ ክልል ለመወዳደር የተመዘገበው የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት ፓርቲ (ኢዲኅፓ) ሊቀመንበር ገብሩ በርሄ ደግሞ ፓርቲው ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
ፓርቲያቸው እስከታች ወርዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት አስቻይ ኹኔታዎች ባሉባቸው አካባቢዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ፓርቲው ከምርጫ ጋር ተያይዞ በማንኛውም ጉዳይ ያለው ዝግጁነት አስተማማኝ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፖርቲ (ኢሕአፓ) የአማራ ክልል አስተባባሪ መሠረት ተሠራ ደግሞ ፓርቲው ከመኢአድ እና እናት ፓርቲ ጋር ምርጫ በተመለከተ በጋራ አብሮ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ትብብር ለኢትዮጵያ የሚል የጋራ ፓርቲ መመሥረቱንም አንስተዋል።
ፓርቲው ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ቀደም ብሎ የቅድመ ዝግጂት ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። ለአብነትም እጩዎችን ማቅረብ እና ማስመዝገብ፣ አስቻይ ኹኔታዎች ባሉባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የመራጮችን ምዝገባ የመመልከት ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በቅድመ ምርጫ ውይይት ላይ ሲነሱ የነበሩ እና ከጸጥታ ኹኔታ ጋር ተያይዞ መንግሥት በደረጃ የለያቸው ቦታዎች ጋር ተያይዞ ስምምነት የተደረገባቸው ጉዳዮች እንዲፈጸሙ የመከታተል ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ የፓርቲውን ማኒፌስቶ የማስተዋወቅ እና ሚዲያዎች የሚያመቻቿቸው የክርክር መድረኮች ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ እንደኾነም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
