እውነተኛ ትስስርን በመፍጠር ሰላምን ማጽናት ይገባል።

15

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት በሰሜን ወሎ ዞን ከቡግና ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም እጦት በማኅበረሰቡ ላይ ጫና እያሳደረ በመኾኑ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ለሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል። የመንገድ፣ የውኃ መሠረተ ልማት እንዲገነባ እና የተጀመረ የሆስፒታል ግንባታ እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው የሃይማኖት አባቶች ለሰላም የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ታጣቂዎች የቀረበውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ማኅበረሰቡ ሊሠራ ይገባል ያሉት አዛዡ የሰላምን አማራጭ በማይቀበሉ ታጣቂዎች ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕግ የማስከበር እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የሰላም እጦት የቡግና ወረዳ ሕዝብ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተጠቃሚ እንዳይኾን አድርጓል ብለዋል። የሆስፒታል ግንባታውን ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት ከኮንትራክተር ጋር ውል በመውሰድ ሥራ እንዲጀምር አቅጣጫ ማስቀመጡንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ ቡግና ወረዳን ከሌሎች ወረዳዎች ጋር የሚያስተሳስር መንገድ በጸጥታ ችግር ምክንያት መቋረጡን ጠቁመዋል።

የመንገድ ሥራው ጥራቱን ጠብቆ እንዲከናወን ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ በቁርጠኝነት ሰላሙን ማጽናት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ማኅበረሰቡ ልጆቹን በመምከር የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ማኅበረሰቡ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ለወረዳው ሕዝብ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሟላት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም አማራጭን ለታጣቂዎች ማቅረቡን ያነሱት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ከታጣቂዎች ጋር ድርድር በማድረግ የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈረሙንም አስታውሰዋል።

ማኅበረሰቡ አደረጃጀትን በማጠናከር እና እውነተኛ ትስስርን በመፍጠር ሰላምን ማጽናት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ሕዝባዊ መንግሥትን በምርጫ በማረጋገጥ ለሰላም እና ልማት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የምርጫ ጣቢያን በተደራጀ መንገድ በመጠበቅ ሰላማዊ ምርጫ እንዲከናወን ማኅበረሰቡ ከልብ መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሕገ ወጥ ነጃጅ አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ ክትትል እንደሚያደርግ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
Next articleበጭልጋ እና አካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ወደሰላም ተመለሱ።