በሕገ ወጥ ነጃጅ አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ ክትትል እንደሚያደርግ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

43

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረውን የተራዘመ ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የነዳጅ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

በዚህም ከነዳጅ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር እና ሽያጭን ለመቆጣጠር እና አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተሠሩ ይገኛሉ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያያ እንዳስታወቀው ወቅታዊውን የነዳጅ እጥረት ተገን በማድረግ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ ለማባባስ እና የሕዝቡን ማኅበራዊ ሕይወት ለማናጋት የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውሮችን ለመከላከል ሰፊ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት እና ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ከፍተኛ ክትትል እና በኬላዎች ላይ በተከናወነ ፍተሻ በርካታ ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር ሙከራዎች መክሸፋቸውም ተገልጿል። በድርጊቱ ላይ የተሠማሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ተገቢውን የሕግ ቅጣት እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቅሷል።

ሕገ ወጥ ድርጊቱ በጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች የሚፈጸም ቢኾንም በሀገር እና በሕዝብ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እጅግ የከፋ መኾኑን ጠቅላይ መምሪያው አመላክቷል። መንግሥት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገባቸው የነዳጅ ምርቶች ለታለመላቸው የልማት ሥራዎች ሳይውሉ መባከን እንደሌለባቸውም ተገልጿል።

ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር እና ሽያጭ የትራንስፖርት ዋጋ እንዲጨምር በማድረግ የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉል እና የሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር በማድረግ የኑሮ ውድነቱን የሚያባብስ ተግባር እንደኾነ አስገንዝቧል።

ከተፈቀደው የዋጋ ተመን ውጭ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ነዳጅ በመደበቅ ሰው ሠራሽ እጥረት የሚፈጥሩ እና ከሕገ ወጥ ነጋዴዎች ጋር የሚተባበሩ ማደያዎች ላይ የማያዳግም አሥተዳደራዊ እና የወንጀል ክስ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቅላይ መምሪያው ገልጿል።

ጨለማን ተገን በማድረግ ነዳጅ ወደተለያዩ ቦታዎች የሚያንቀሳቅሱ፣ በማከማቸት ለጥቁር ገበያ የሚያዘጋጁ እና በማደያዎች ላይ በኃይልም ኾነ በማግባባት ነዳጅ የሚያስቀዱ አካላት ላይ ያለ ምንም ምህረት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ጠቅሷል ።

የነዳጅ እጥረቱን ተከትሎ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ሕዝብን ለእንግልት የሚዳርጉ አካላትን በምንም ዓይነት ሁኔታ ፖሊስ አይታገስም ነው ያለው ጠቅላይ መምሪያው።

አሁን ላይ ፖሊስ የኬላ ቁጥጥሩን ከወትሮው በተለየ በማጠናከር የነዳጅ ሥርጭቱ ሕጋዊ መስመር መያዙን ለማረጋገጥ ሌሊት እና ቀን እየሠራ እንደሚገኝም ገልጿል።

የክልሉ ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት የሚጠበቀው በጋራ በሚደረግ ጥረት ነው ያለው ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያው ኅብረተሰቡ ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት በመጸየፍ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ለቅርብ ፖሊስ ጣቢያ በመጠቆም የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምሁራን የጥፋት መንገድን በማውገዝ ችግሮች በንግግር እና በአመክንዮ እንዲፈቱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
Next articleእውነተኛ ትስስርን በመፍጠር ሰላምን ማጽናት ይገባል።