ምሁራን የጥፋት መንገድን በማውገዝ ችግሮች በንግግር እና በአመክንዮ እንዲፈቱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

24

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፣ የልማት አርበኛም እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።

በምክክር መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። መንግሥት ለሰላማዊ አማራጭ አሁንም በሩ ክፍት ነው ብለዋል።

የሰላም አማራጭን ተቀብለው ለመጡ አካላት ወደ ተረጋጋ ሕይወት እንዲገቡ እየተደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል። የውጭ ኀይሎችን አጀንዳ ተቀብለው ሰላምን የማይቀበሉ ኀይሎችን በጋራ ማውገዝ እና መታገል ይገባልም ነው ያሉት።

ምሁራን የጥፋት መንገድን በማውገዝ፤ የሰላም አማራጭን በማንገስ፤ የተደናገሩትን በመመለስ፤ በውይይት፣ ችግሮች በንግግር እና በአመክንዮ እንዲፈቱ በማድረግ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የውጭ እና የውስጥ ኀይሎች በከተማዋ በተደጋጋሚ ሰላም እንዳይፈጠር ቢሠሩም በሕዝቡ፣ በጸጥታ ኀይሉ እና በመሪዎች ጥረት ሰላሟ ተጠብቋል ነው ያሉት።

ምሁራንም ሕዝብ እና ሀገር የሚቀይር ሀሳብ በማምጣት ለዘላቂ ሰላም መሥራት እንደሚገባቸው አንስተዋል። ከመንግሥት ጎን በመቆም የሰላም ግንባታን መደገፍ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ተግባራት በተጨማሪ አካባቢያዊ፣ ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ክልሉ ካጋጠመው ችግር እንዲወጣ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል። የዩኒቨርሲቲው ምሁራንም በታሪክ እና በትውልድ የተጣለባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል።

ሀገር እና ወገን ችግር ውስጥ ሲወድቁ ምሁራን ከዝምታ ወጥተው ለሰላም፣ ለልማት እና ለዕድገት መሪ ተዋናይ መኾን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleበሕገ ወጥ ነጃጅ አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ ክትትል እንደሚያደርግ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።