የፍትሕ እና የዳኝነት ሥርዓቱን በማዘመን ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል።

12

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት የ18ኛ ዙር ዕጩ አቃቢያን ሕግ እና የዳኞች የቅድመ ሥራ ሥልጠና የማስጀመሪያ መርሐ ግብርን አካሂዷል።

የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንሰቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) የሪፎርም ሥራዎችን በማጠናከር የፍትሕ እና የዳኝነት ሥርዓቱን በማዘመን ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ሠልጣኞች በሕግ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቀስመው የመጡትን ክህሎት የበለጠ ሊያሳድግ የሚችል ሥልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ሥልጠናው ማኅበረሰቡ ከዳኝነት እና ከፍትሕ ሥርዓቱ የሚጠብቀውን አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ያደርጋል ነው ያሉት።

ለሠልጣኞች የክህሎት፣ የሥነ ምግባር እና የዕውቀት ሥልጠና በተጨማሪ የተግባር ልምምድ ይሰጣል ብለዋል።

አዳዲስ ተጨማሪ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሠልጣኞች ለሙያቸው ብቁ፣ ለሥራቸው ታታሪ እና ታማኝ ኾነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ይህም ማኅበረሰቡ በፍትሕ እና በዳኝነት ሥርዓቱ ያለውን ዕምነት እንዲያሳድ ያግዛል ነው ያሉት።

ዕጩ ሠልጣኞች በሥነ ምግባር ታንጸው የፍትሕ ሥርዓቱን እንዲቀላቀሉ እና በቅንነት ሙያዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያችል መኾኑን ነው የገለጹት።

ዕጩ ሠልጣኞች የተሻለ ዕውቀት በመቅሰም በማኅበረሰቡ የፍትሕ ሥርዓትን ለማረጋገጥ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በዳኝነት ዘርፍ የሚሰለጥኑት ረድኤት ሰሀሉ የቀሰሙትን የንድፈ ሀሳብ ትምህርት በማዳበር ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ የሚሰጠውን ሥልጠና በአግባቡ ለመውሰድ እና ሙያዊ ሥነ ምግባርን በመላበስ ማኅበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው በአቃቢያን ሕግ ዘርፍ የሚሠለጥኑት ጌትነት ዓለምነህ በዘርፉ የሚሰጠውን የቅድመ ሥራ ሥልጠና በአግባቡ ለመከታተል ዝግጁ መኾናቸውንም አስረድተዋል።

ከሙስና እና ከብልሹ አሠራር በመጽዳት በቅንነት እና በታማኝት በማገልገል ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በሥልጠናው 300 የሚኾኑ ዕጩ አቃቢያን ሕግ እና ዳኞች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ሥራዉድንቅ ደሳለው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዜጎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመምረጥ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል።
Next article“ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ