ዜጎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመምረጥ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል።

9

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለው ቅቡልነት የሚረጋገጥበት ሁነኛ መሣሪያ ነው።

አንድ ሀገረ መንግሥት በዜጎች ዘንድ ቅቡልነት እንዲኖረው ከሚያስችሉት መንገዶች አንዱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መከተሉ ነው። የዴሞክራሲ ልምምድ አንዱ መገለጫ ደግሞ ምርጫን በፍትሐዊነት እና በታማኝነት በወቅቱ ማስኬድ ነው።

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ኑሩ አሕመድ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር የሚፈጸምበት መሣሪያ ነው ብለዋል።

ምርጫ በመጣ ወቅት የሚታየው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ነው ያሉት መምህሩ፤ ይህ ደግሞ በፖለቲካ ሳይንስ የሕዝብ ድምጽ ዋጋ እንዳይኖረው፣ የሕዝብ ድምጽ በየሠፈሩ እንዲበተን ወይም እንዲባክንም ያደርገዋል ነው ያሉት። ይህ ባሕል መሻሻል እንዳለበትም አንስተዋል።

እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ ያሉ ያደጉ ሀገራት የሁለት ፓርቲ ሥርዓት ነው የሚከተሉት። እነዚህ ሀገራት የዕድገት መሠረታቸውም የፓርቲዎች ቁጥር ማነስ እና ዜጎች በምርጫ በሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ እንደኾነም ጠቁመዋል።

በእኛ ሀገርም ቢኾን ሦስት ወይም አራት ጠንከር ያሉ ፓርቲዎች ቢወዳደሩ ሀገራዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ እንደኾነም አስገንዝበዋል።

“በምርጫ የነቃ ተሳትፎ አለማድረግ ብሔራዊ ጥቅምን እንደሚጎዳ ያነሱት” የፖለቲካ ምሁሩ ዜጎች ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን የመምረጥ መብት በመጠቀም ድምጽ መስጠት እንዳለባቸው መክረዋል።

ገዥው ፓርቲም ኾነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዜጎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን ከወዲሁ መሥራት እንዳለባቸውም መክረዋል።

በቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰርኩላር ኢኮኖሚ ሞዴል ፋይዳ እና የኢትዮጵያ ተሞክሮ።
Next articleየፍትሕ እና የዳኝነት ሥርዓቱን በማዘመን ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል።