ፉክክር እና ትብብርን በሚዛን በማየት ሀገርን በማስቀደም መንቀሳቀስ ይገባል።

2

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ፓርቲውን ወክለው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ እጩዎች የትውውቅ መድረክ አካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ለብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለጋስ እና የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ሰላማዊት ዓለማየሁ በቀለ ደግሞ ለፓርቲው የክልል ምክር ቤት በባሕር ዳር ከተማ ዕጩ ኾነው ቀርበዋል።

በትውውቅ መድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ብልጽግና በችግር ወቅት ተወልዶ ሀገርን ከችግር ያላቀቀ ፓርቲ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኃላ ቀር፣ ድሃ እና ሙስና የተንሰራፋባት ኾና እንድትታወቅ የሚሠሩ አካላት ተወግደው የሀገር ክብር እንዲመለስ ብዙ የሠራ ፓርቲ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

የውስጥ ባንዳ እና የውጭ ባዳዎች በሚሰጡን አጀንዳ የሚፈጠሩ የጥላቻ ትርክቶች ውድቅ እንዲኾኑም ፓርቲው በትኩረት ሠርቷል፤ ሀገራዊ አንድነት እና ልማት እንዲመጣም አስችሏል ነው ያሉት።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ባሕር ዳር ከተማን ወክለው የሚሳተፉ ዕጩዎችም ኢትዮጵያ የምትኮራባቸው ዕንቁ ልጆቻችን በመኾናቸው ተደስተናል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህም ኾኑ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለሀገር መሰዋዕትነትን እስከመክፈል ድረስ ዝግጁ ኾነው የሠሩ፣ ለሀገራቸው ያለረፍት ሠርተው ተጨባጭ ለውጥን ያሳዩ ቆራጥ መሪዎች ናቸው ነው ያሉት። አሁን ላይ የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ የኾኑት ወይዘሮ ሰላማዊት ዓለማየሁም ቢኾኑ በተለያዩ ተቋማት በአመራርነት ሀገር እና ሕዝብን ያገለገሉ ጀግና ሴት መኾናቸውን ገልጸዋል።

ምርጫ ዋነኛው የዴሞክራሲ መገለጫ ነው ያሉት አስተባባሪው ሕዝቡም በምርጫ መሳተፍ፤ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ መሪዎቹን መምረጥ እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መኾን አለበትም ብለዋል። ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ ሀገረ መንግሥት ማጽናት እና ታላላቅ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማሳካት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

ጠብ አጫሪነት ለማንም አይበጅም፤ የሥልጣን ስስትንም ወደኃላ በመተው ለሀገር ህልውና ቅድሚያ መስጠት ይገባል ብለዋል። ፉክክር እና ትብብርን በሚዛን ማየት እና አንዲት ሀገራችንን አስቀድመን መንቀሳቀስ አለብን ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፉክክር እና ትብብርን በሚዛን በማየት ሀገርን በማስቀደም መንቀሳቀስ ይገባል።