“ሀገር እና ሕዝብ ቸገረኝ ባለ ጊዜ ቀድመው የሚገኙ የቁርጥ ቀን ልጆች በከተማዋ ውስጥ ዕጩ ኾነው ቀርበዋል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

30

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ፓርቲውን ወክለው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ እጩዎች የትውውቅ መድረክ እያካሄደ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ለብልጽግና ፖርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለጋስ እና ወይዘሮ ሰላማዊት ዓለማየሁ በቀለ ደግሞ ለፓርቲው የክልል ምክር ቤት በባሕር ዳር ከተማ ዕጩ ኾነው ቀርበዋል።

በትውውቅ መድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሀገር እና ሕዝብ ቸገረኝ ባለ ጊዜ ቀድመው የሚገኙ የቁርጥ ቀን ልጆች በከተማዋ ውስጥ ዕጩ ኾነው ቀርበዋል ነው ያሉት።

የቀረቡ እጩዎች ለክልሉም ኾነ ለሀገራችን ምልክት የኾኑ፤ በሀቀኝነት ቆመው ሀገር እና ሕዝብን የማገልገል መልካም ዝና ያላቸው እና ታታሪዎች ናቸው ብለዋል።

ዕጩዎቹ ክልሉ የጸጥታ ችግር በገጠመው ጊዜ ሁሉ በቁርጠኝነት እና መስዕዋትነትን በሚጠይቁ ሁኔታዎች ጭምር ተጋፍጠው ለሰላም መስፈን የሠሩ፤ በተግባርም ውጤት ያመጡ እና ሕዝብ እፎይታ እንዲያገኝ ያስቻሉ መኾናቸውን ገልጸዋል።

እንዲህ አይነት ጉምቱ መሪዎች በባሕር ዳር ዕጩ ኾነው መቅረባቸው ለከተማዋ ሕዝብም ኩራት ነው ብለዋል።

የእጩዎችን የሥራ ልምድ እና የቀደመ የመሪነት ታሪክ ያቀረቡት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን እጩዎች በዕውቀት እና በሥራ ልምድ የበቁ፣ ከአማራ ክልልም አልፈው ለሀገር ኩራት የኾኑ ናቸው ብለዋል።

ባሳለፉት የመሪነት ጊዜ ሁሉ ችግሮችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሀገርን ለለውጥ ያበቁ፣ አስጨናቂ ችግሮች ሁሉ ተወግደው የተስፋ ብርሃን እንዲፈነጥቅ የሠሩ እና እየሠሩም ያሉ ናቸው ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመንግሥት ሠራተኞች አንድነት እና ፍትሐዊነትን በማጠናከር ለሕዝብ ውጤታማ ተግባር መከወን አለባቸው።
Next articleየኢትዮ- ሩሲያ መሪዎች የስልክ ውይይት።