
ባሕር ዳር: መጋቢት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት በሰሜን ወሎ ዞን ከላሊበላ ከተማ አሥተዳደር እና ከላስታ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ተወያይተዋል።
መንግሥት ሰላምን በዘላቂነት እንዲያሰፍን የውይይቱ ተሳታፊዎች በአጽንኦት አንስተዋል። የክልሉ መንግሥት በዞኑ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በጥራት እያከናወነ በመኾኑም አመስግነዋል። በፍጥነት እንዲጠናቀቁም ጠይቀዋል። ሰላምን ለማምጣት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ተናግረዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ለክልሉ ሕዝብ ሰላም መስዋዕትነት እየከፈሉ መኾኑን ተናግረዋል። መሠረተ ልማቶች እንዲፋጠኑ ሰላም አስፈላጊ በመኾኑ ሰላምን ማጽናት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የሰላም እጦት የሰብዓዊ ጉዳትን ከማድረስ ባሻገር የዞኑ የልማት ሥራዎች በታቀደላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ፤ የኑሮ ውድነት እንዲኖር፤ ሥራ አጥነት እንዲስፋፋ እና ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲበራከቱ አድርጓል ብለዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ የሰላም እጦቱ የቅዱስ ላሊበላ ቅርስ ጥገና እንዳይደረግለት እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል። የመንግሥት ሠራተኞች ሀገር እና ሕዝብን በማስቀደም ለሰላም የበኩላቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ልትሠሩ ይገባል ብለዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻችሁን ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ብልሹ አሠራርን በማስቀረት ሕዝብን በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባ ተናግረዋል። የተጀመሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሰላም እጦቱ በከተማው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ጫና ማሳደሩን የተናገሩት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ከተማው ከቱሪዝም ገቢ እንዲያገኝ፤ የቅዱስ ላሊበላ ቅርስ ጥገና እንዲደረግለት ሰላምን ማጽናት አለባችሁ ብለዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች አንድነት እና ፍትሐዊነትን በማጠናከር፤ ቁልፍ የመንግሥት አገልግሎቶችን በመምራት ለማኅበረሰቡ ውጤታማ ተግባር እንዲያከናውኑም አሳስበዋል። የምርጫ ካርድ በማውጣት፤ በመምረጥ፤ ፍትሐዊ፤ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ምርጫ እንዲከናወን ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫን በማከናወን የሚበጅ መንግሥትን መትከል ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
