ለጥንቃቄ

6

 

ባሕር ዳር:መጋቢት 07/2018 ዓ.ም
ከፍተኛ ሙቀት የሚመዘገባቸው አካባቢዎች እና መደረግ ያለበት ጥንቃቄ፦

በኢትዮጵያ ሚትርዮሎጂ ኢንስቲትዩት የምዕራብ አማራ ሜትርዮሎጂ አገልግሎት ማዕከል በአማራ ክልል አንዳንድ ዞኖች ከፍተኛ የሙቀት መጠን ሊመዘገብ እንደሚችል አስታውቋል።

የማዕከሉ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን አሥተባባሪ እንደግ አንለይ ወቅቱ በልግ በመኾኑ ምሥራቃዊ አማራ ዝናብ የሚያገኝበት፣ ምዕራቡ ደግሞ በአብዛኛው ደረቅና ፀሐያማ የአየር ፀባይ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በዚህ ወቅት በዓመቱ ከፍተኛ የሙቀት መጠን የሚመዘገብበት ጊዜ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ውስጥ በምዕራብ ጎንደር፣ በተወሰኑ ማዕከላዊ ጎንደርና የጃዊ አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ ከ38 እስከ 39 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊደርስ እንደሚችል አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

በተለይም እንደ ሽንፋ፣ መተማ፣ ቋራ እና አብሃጅራ በመሳሰሉት ዝቅተኛ ሥፍራዎች የሙቀት መጠኑ እስከ 41 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ ሊል እንደሚችል ትንበያዎች ያሳያሉ ነው ያሉት። በአንዳንድ ሥፍራዎች ደግሞ ሙቀቱ እስከ 43 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊደርስ ይችላል። ከፍተኛ ሙቀቱ እስከ ሚያዝያ ወር መጨረሻ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ለከፍተኛ ሙቀቱ መፈጠር አንደኛው ምክንያት የፀሐይ አቅጣጫ ኾኖ ተቀምጧል። ወቅቱ ፀሐይ ከደቡብ ንፍቀ ክበብ ወደ ሰሜን ንፍቀ ክበብ የምትጓዝበት ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ከምድር ወገብ ከቅራቢያ ስለምትገኝ በዚህ ወቅት ለከፍተኛ ሙቀቱ እንድትጋለጥ ያደርጋታል ብለዋል አስተባባሪው።

ሌላኛው ምክንያት አብዛኛዎቹ የምዕራብ አማራ አካባቢዎች ከባሕር ጠለል በላይ ከ8 መቶ እስከ 1 ሺ ሜትር ብቻ ከፍታ ያላቸው ቆላማ በመኾናቸው ለከፍተኛ ሙቀት እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል።

አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ደመናዎችም ከመሬት የሚነሳው ሙቀት ወደ ላይ እንዳይወጣ አምቀው በመያዝ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ሙቀት (ወበቅ) እንዲፈጠር ማድረጋቸውን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ሙቀቱ የሰውነት ፈሳሽ መጠን መቀነስ (ድርቀት)፣ ድካም፣ ራስ ምታት፣ ራስን መሳት፣ ስትሮክ የመሳሰሉትን በሽታዎች በሰው ላይ ሊያስከትል ይችላል። የመሬት ውስጥ እርጥበትና ውኃ መጠንን በመቀነስ ቋሚ ተክሎች የመድረቅ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል።

በእንስሳት ላይም የወተትና የሥጋ ምርት መቀነስ እንዲኹም የውኃ ፍላጎት መጨመርን ተከትሎ የውኃ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል አቶ እንደግ ጠቅሰዋል።

ኅብረተሰቡ ምን ማድረግ አለበት?

-አንድ ሰው በቀን 2 ሊትር እና ከዚያ በላይ ውሃ መጠጣት፤

-ከፍተኛ ሙቀት በሚመዘገብባቸው አካባቢዎች የቀትር ሰዓታት እረፍት በማድረግ፣ ሥራዎችን በጠዋት እና በማታ (ሙቀት በማይበዛባቸው ሰዓታት) ማከናወን፤

-የፀሐይን ጨረር ወደ ኋላ መመለስ የሚችሉ ነጭ እና ቀለል ያሉ (ስስ) ልብሶችን መልበስ፤

-ዛፍ ጥላ ሥር እና በቂ አየር በሚዘዋወርባቸው ቦታዎች መምረጥ እናና ጊዜን ማሳለፍ እንደሚገባ አሥተባባሪው መክረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተወያዩ።
Next articleየመንግሥት ሠራተኞች አንድነት እና ፍትሐዊነትን በማጠናከር ለሕዝብ ውጤታማ ተግባር መከወን አለባቸው።