
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ የክልሉ የሰላም ሁኔታ በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
ዶክተር እሸቱ እንዳሉት ታጣቂዎች ግጭትን ለማባባስ በቅርቡ ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ሙከራቸው እንዳልተሳካለትም ተናግረዋል። ጽንፈኛው ቡድን ሻቢያ እና የከሰመውን ህወሃት ርዝራዦች ጦርነት ሲከፍቱ እኔ ከመሐል ያለውን አጠቃለሁ ብሎ የያዘው የረጅም ጊዜ ዕቅድ እንደከሸፈበትም አንስተዋል።
በተለይም በደቡብ ጎንደር እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ላይ ጉዳት ለማድረስ መንቀሳቀሱን አስታውሰዋል። ነገር ግን በጸጥታ ኀይሉ በደረሰበት ምት ያሰበውን ማሳካት አልቻለም ነው ያሉት። የክልሉ የጸጥታ ኀይል በጽንፈኛው ላይ እርምጃ በመውሰድ አቅሙን እንዳሳየውም ተናግረዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ግፍን በመቃወም ጽንፈኛ ቡድኑን እየታገለ ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ አታዋጡኝም፣ ችግሬን እያባባሳችሁ ነው፤ ልጄቼ እንዳይማሩ እያደረጋችሁ ነው በማለት ምሬቱን እየገለጸላቸው ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ የጽንፈኛውን እኩይ ዓላማ በሚገባ መረዳቱንም ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን የተናገሩት ኀላፊው የሃይማኖት አባቶች ለሰላም እሴት ግንባታ ዋና ናቸው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተናግረዋል። ኅብረተሰቡን የማስተሳሰር ሚናቸውም ትልቅ ነው ብለዋል። የተደረገው ውይይት ተቀራርቦ ለመሥራት እና ሰላምን በጋራ ለማጽናት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።
የክልሉ የጸጥታ ኀይል የመፈጸም አቅሙን እያሳደገ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው በየጊዜው ለጸጥታ ኀይሉ ሥልጠና እየሠጡ፣ ቁጥሩን እየጨመሩ እና አደረጃጀቱን እያጠናከሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የክልሉ የጸጥታ ኀይል ጠላትን ተዋግቶ ድል የሚያደርግ ነው ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊትም የክልሉን የጸጥታ ኀይል እየደገፈ እና እያጠናከረ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
የክልሉ የጸጥታ ኀይል ጽንፈኛው ሀገር አውዳሚ እንደኾነ፣ ሕዝብን ለችግር እንደሚዳርግ እና ክልሉን እንደሚያዳክም በውል የተረዳ ነው ብለዋል። የጽንፈኛው ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶች አጀንዳ የሚቀበል እና የእነርሱን አጀንዳ የሚቀበል እንደኾነ በመረዳት አምርሮ እየታገለ ነው ብለዋል። ለክልሉ የጸጥታ ኀይል ክብር እና ምሥጋና እንደሚገባውም ገልጸዋል።
የሰላም ሞተሩ ሕዝብ ነው ያሉት ኀላፊው ሕዝብ ለሰላም ያለው ሚና ተኪ የለውም፤ የሚያጠፋውን ተው ማለት፤ ማስተካከል እና መገሰጽ ይችላል ነው ያሉት።
ሕዝቡ ለሰላም እያሳየው ባለው ተነሳሽነት የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ እንዲመጣ አስችሏል ብለዋል። ኅብረተሰቡ ለጸጥታ ኀይሉ መረጃ እያቀበለ እና ጽንፈኛው ቡድን ከጠላቶች ጋር እንደሚሠራ በመረዳቱ ጽንፈኛውን እየታገለው ነው ብለዋል። ከዚህ የበለጠ ጽንፈኛውን አምርሮ ሊታገለው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የፖለቲካ መሪዎችም መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሕዝብ ሰላም መሥራታቸውን ተናግረዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችም የሰላም አማራጭን ተቀብለው መግባታቸውን አንስተዋል።
አሁንም የክልሉ መንግሥት የሰላም አማራጭን የሚቀበሉ ታጣቂዎችን ለመቀበል ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል። የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች ወደ ቀደመ ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን እና ሥራ ላልነበራቸው ደግሞ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ነው የገለጹት።
የክልሉ መንግሥት የሰላም አማራጭን የሚቀበሉ ኀይሎችን እንደጠላት አይመለከትም፤ ይልቅስ በእንክብካቤ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እየመለሰ ነው ብለዋል። ጥያቄን በጦርነት ለማስመለስ የሚደረግ አካሄድ አውዳሚ እና አክሳሪ መኾኑንም ገልጸዋል። ችግሮችን በውይይት መፍታት ዘመኑ የሚጠይቀው አማራጭ መኾኑንም አንስተዋል።
ግጭት የአማራ ክልል ሕዝብን እየጎዳ ከመሄድ ውጭ ያመጣው ለውጥ የለም ነው ያሉት።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ጽንፈኛው ቡድን የትኛውንም አይነት አማራጭ ተጠቅሞ ግጭት ለመፍጠር ቢሞክርም ሕግ እያስከበርን ምርጫ እናካሂዳለን፤ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል፣ አቅም፣ ብቃት እና ዝግጅት አለን፤ ይህ አይቀርም ነው ያሉት። ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ የጸጥታ ኃይሉ ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል። ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኹነቶችን እያካሄደ የመጣ ክልል ምርጫን ለማካሄድ አይከብደውም ነው ያሉት።
አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሁሉም ትስስር እና ቅንጅት ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊው ሰላም የሚረጋገጠው ችግሮችን በውይይት በመፍታት ነው ብለዋል። ማንኛውም አካል ጥያቄ አለኝ ካለ ወደ ጠረጴዛ ይዞ ይምጣ፤ ሰላም የሚመጣው በውይይት ነው ብለዋል።
ሰላም የሚመጣው በአንድነት፣ በመተባበር ነው፤ አንድ ስንኾን እንጠነክራለን፤ ኢኮኖሚውን እናሳድጋለን ያሉት ኀላፊው መበታተን አቅም የሚያሳንስ እና ለጠላት የሚያጋልጥ ነው ብለዋል። ክልሉን ለማልማት መፍትሔው መሠባሠብ እና በአንድነት መቆም መኾኑንም ተናግረዋል።
ወጣቶች ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው ለሰላም እና ለሀገር ዕድገት እንዲሠሩም አሳስበዋል። ግጭትን የሚያባብሱ ሚዲያዎችም ከድርጊታቸው መቆጠብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
