የያዙት የምርጫ ካርድ የተሻለች ነገን ለመወሰን እንደሚያስችላቸው የመተማ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

3

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ለአንድ ወር እንደሚካሄድ ማስታወቁ ይታወሳል። ዜጎችም የመራጮች ምዝገባን እያካሄዱ ነው።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ነዋሪዎችም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የቀጣይ መሪያቸውን የሚወሱንበት የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ነዋሪዎቹ ምርጫ የሀገርን ሕልውና ለማስቀጠል ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በክልሉ እየተስተዋለ ያለው ችግር መቆም የሚችልበት መንገድ ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት። ይህን ማምጣት የሚቻለው ደግሞ በአፈሙዝ ሳይኾን በምርጫ ካርድ መኾኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በተፈጠረው ጦርነት ሃብት ንብረት ከመዘረፉ እና ከመውደሙ ባለፈ ዜጎች ለሕልፈት እና ለስደት እየተዳረጉ ነው፤ እንዲህ ባለበት ክልል ምርጫ ማካሄድ ፖለቲካዊ ቅንጦት ሳይኾን የሕልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

ከዚህ ችግር ማውጣት የሚያስችል ጠንካራ የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ካርድ መምረጥ ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል።

የጤና፣ የትምህርት፣ የመንገድ እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍትሐዊነት እና በእኩልነት ተደራሽነትን ሊያረጋግጥልን የሚችል መንግሥት በምርጫ ካርድ ለመምረጥ ዝግጁ ነን ብለዋል።

ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ በዜጎች መካከል መከባበር እና መተሳሰብ እንዲጎለብት፣ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ማንነቱ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዲከበር የሚያስችል መሪ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የመራጮች ካርድ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ እንዲኾን አሥፈጻሚ አካላት በትኩረት መሥራት አለባቸው ብለዋል።

የሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮችን ለማረጋገጥ እና ከችግሮች ለመውጣት የሚያስችል ጠንካራ መንግሥት አስፈላጊ ነው፤ የሚበጀንን ፓርቲ ለመምረጥም የመራጮች ካርድ ወስደናል ነው ያሉት።

የምርጫ ካርድ ለፖለቲካዊ የፉክክር ፍጆታ የሚውል ሳይኾን የነገ የዜጎች እጣ ፈንታን የሚወሰንበት መሳሪያ እንደኾነም አንስተዋል።

ለሀገር ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ልማት ይጠቅማል የሚሉትን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡

የያዙት የምርጫ ካርድ የተሻለች ነገን ለመወሰን እንደሚያስችላቸው ተስፋ ማድረጋቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ ሁሉም ዜጋ የመራጭነት ካርድ መውሰድ እንዳለበትም አንስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመረጃ ሀብት የሚኾነው ትክክለኛነቱ ሲረጋገጥ እና በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውል ነው።
Next article“የሰላም ሞተሩ ሕዝብ ነው” እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)