
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነች ትገኛለች። ይህ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅም እየተሠራ ይገኛል።
ይህን በማድረግ ረገድ በተለይ መገናኛ ብዙኅን ትክክለኛ መረጃን ለሕዝብ በማድረስ የማይተካ ሚና ይጫወታሉ። በአንጻሩ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ደግሞ የምርጫን ተዓማኒነት በማሳጣት በዴሞክራሲያዊ ሂደት እና በሕዝብ ሰላም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት መምህር ነገሠ በላይ (ዶ.ር) ምርጫ የራሱ የኾነ የአዘጋገብ ሂደት እንዳለው ገልጸዋል። በምርጫ ወቅት ሚዲያዎች የራሳቸው የተለየ ሚና እንዳላቸውም ጨምረዋል። ኅብረተሰቡ ስለ ምርጫ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኝ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያነሱት።
አሁን ላይ መረጃ ሰጭው እና ተቀባዩ የተደበላለቀበት ጊዜ ላይ ነን ያሉት ዶክተር ነገሠ መረጃ ሰጭው ሁሉም ሲኾን ሀሰተኛ መረጃ እንዲስፋፋ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት። የመረጃ ምንጭን ያለመለየት ችግር እንደሚስተዋልም ጨምረው ተናግረዋል።
እንደ መምህሩ ገለጻ ሀሰተኛ መረጃ በፍጥነት በተስፋፋ እና ተደራሽነቱ በሰፋ ቁጥር በኅብረተሰቡ እና በሚዲያዎች መካከል አለመተማመን ይፈጠራል። ትላልቅ መገናኛ ብዙኅን መረጃዎችን በፍጥነት ለኅብረተሰቡ በማድረስ ኅብረተሰቡ በቂ መረጃ እንዲያገኝ እንዲሁም የኅብረተሰቡን ዕውነት በመዘገብ ሕዝቡን ከሀሰተኛ መረጃ መከላከል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ሚዲያዎች መረጃን በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ፣ ተዓማኒነታቸውን ማረጋገጥ እና መረጃዎች ብዙኀኑን የሚጠቅሙ መኾናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በምርጫም ኾነ በማንኛውም ጊዜ መረጃን ከማን እና እንዴት ማግኜት እንዳለበት ጠንቅቆ ሊያውቅ እንደሚገባ አስረድተዋል።
መረጃዎችን መዝኖ ማየት እና መውሰድ እንዳለበትም መክረዋል።
የሚያነባቸውን፣ የሚያዳምጣቸውን እና የሚመለከታቸውን መረጃዎች መመዘን ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ ከስሜት መውጣት ይኖርበታል ያሉት መምህሩ በሁሉም ዘንድ ሚዛናዊ የኾነ ጆሮ እና ዐይን ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
መረጃ ሀብት የሚኾነውም ከትክክለኛው የመረጃ ምንጭ በትክክለኛው መንገድ መጠቀም ሲቻል መኾኑንም ተናግረዋል።
የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት መምህሩ ዶክተር ነገሠ ኅብረተሰቡ የሚዲያን ሚና ሊረዳ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሚዲያን ያለአግባብ ከተጠቀምንበት ኅብረተሰቡን ወደ ግጭት እና ጥፋት ስለሚያስገባ በጥንቃቄ እና ኀላፊነትን ይሻል ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ ሚዲያ አምላኪም፤ ሚዲያ ጠልም መኾን እንደሌለበትም ነው ዶክተር ነገሠ መልዕክት ያስተላለፉት። ይልቁንም በሚዛን ላይ ቆሞ ለሕዝብ እና ለሀገር የሚበጅ መረጃ የሚያቀርቡትን መገናኛ ብዙኅን መለየት፣ የተገኙ መረጃዎችንም በአግባቡ መጠቀም ይገባል ሲሉ መክረዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
