
ባሕር ዳር: መጋቢት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ)በኮሪደር ልማት የሀረር ከተማን ታሪክ እና ቀደምት ሥልጣኔ የሚመጥኑ ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን የሀረሪ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሔኖክ ሙሉነህ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት ማኅበረሰቡን በማስተባበር በኮሪደር ልማት ሥራዎች የሀረር ከተማን የቀድሞ ገፅታ የቀየሩ ተግባራት ማከናወኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ ሀረር ቀደምት ሥልጣኔዋን በሚመጥን ደረጃ ላይ እንድትገኝ እና ሀረር ታሪካዊ ከተማ ብቻ ሳትኾን ከዘመኑ ጋር የምትዘምን እንድትኾን ያስቻሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ የአካባቢውን ፀጋና ዐቅሞችን መነሻ ባደረገ መልኩ በአነስተኛ ወጪ፣ በላቀ የአመራር ጥበብ እና ቁርጠኝነት ሕዝብን በማስተባበር የተከናወነ እንደኾነም ተናግረዋል።
በዓለም አቀፉ ቅርስ የጁገል ግንብ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች 25 ኪሎ ሜትር፣ በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች 15 ኪሎሜትር፣ በገጠር ወረዳዎች 50 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
የኮሪደር ልማቱ የተሽከርካሪ፣ የብስክሌት እና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ አረንጓዴ ሥፍራዎችን፣ ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራቶችን ባካተተ መልኩ የተከናወነ እና ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ውብና ማራኪ እንድትኾን አስችሏል ብለዋል።
ልማቱ በመደመር መንግሥት ዕሳቤ ፈጠራን፣ ፍጥነት እና ጥራትን መሰረት ባደረገ መልኩ የተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። የከተማውን ውበት የገለጡ እና በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ዐቅም ለመጠቀም እያስቻሉ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በተለይ በከተማ እና በገጠር በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል።
ከፅዳት መጓደል ጋር በተያያዘ ሲስተዋሉ የቆዩ ችግሮችን በመቅረፍ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራው በርካታ ተሞክሮዎች የተገኙበት፤ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በፍጥነት የመጨረስ ልምድ እና በጋራ በመሥራት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጥሩ ተሞክሮ የተገኘበት መኾኑንም አንስተዋል።
የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎችና የታዩ ውጤቶችም የሀረርን ገናናነት ዳግም እውን ማድረግ እንደሚቻል አመላካች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከሀረሪ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ ሀረር ታሪክ እና ቀደምት ሥልጣኔዋን በሚመጥን ደረጃ በብልጽግና ምዕራፍ ላይ እንድትገኝ እያስቻሉ ናቸው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
