
ደብረብርሃን፡ መጋቢት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሚያ ክልል ሸኖ ከተማ አሥተዳደር እና የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጎራባች ወረዳዎች ነዋሪዎች በአብሮነት እና በሰላም ጉዳይ ላይ መክረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ ሰላምን በማጠናከርና የጋራ ኢኮኖሚን በመገንባት የነዋሪዎችን የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ሥራ ይሠራል ብለዋል።
ዕሴቶችን በማጠናከር የቀደመውን አብሮነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሠራልም ነው ያሉት።
በሸኖ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀብታሙ አብደታ የሰላምን ዋጋ ያልተረዱ እና የሀገር ፍቅር ለጎደላቸው ግለሰቦች ሀሳብ ማስፈጸሚያ ባለመኾን የአካባቢን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሕዝብን የሚከፋፍሉ እና የሥነ ምግባር ዝንፈት ያለባቸውን መሪዎች የማረም ሥራ እንደሚሠራም አንስተዋል።
የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሰላም እና አንድነትን ማጠናከር ይገባል ያሉት ደግሞ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሩ ኮሎኔል አደራጀው ሰረበ ናቸው።
ሰላም ጠል የኾኑ ግለሰቦችን ለማረቅ በሚደረገው ሥራ ሁሉ የጸጥታ መሪዎች ድጋፍ ያደርጋሉ ብለዋል።
በሕዝብ ስም የሚነግዱ የሀገር ባንዳዎችን ማረም የጋራ ሥራ መኾን እንዳለበትም አሰገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም እንደ ድር እና ማግ የኾነውን የኦሮሚያ እና የአማራ ተወላጅ ለመከፋፈል የሚደረገውን የጥላቻ ዘመቻ ማስቆም ላይ ሚናቸውን እየተወጡ መኾኑንም ተናግረዋል። በፍቅር እና በአንድነት በመቆም የሀገርን ሰላም እና ልማት ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
በአጎራባች አካባቢዎች ያሉ የሕግ ማስከበር ሥራዎች በአግባቡ መሠራት እንደሚገባቸው ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች በመግባቢያ ቋንቋ ብንለያይም የጋራ አብሮነት እና ሰላምን ለማስቀጠል እንሠራለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
